1 የዮሐንስ መልእክት 1:1-10

1 የዮሐንስ መልእክት 1:1-10 አማ05

ከመጀመሪያው ስለ ነበረው ስለ ሕይወት ቃል እንጽፍላችኋለን፤ ይህ የሕይወት ቃል የሰማነውና በዐይኖቻችን ያየነው፥ የተመለከትነውና በእጆቻችን የዳሰስነው ነው። ይህ ሕይወት ተገልጦአል፤ እኛም አይተነዋል፤ እንመሰክራለንም። በአብ ዘንድ የነበረውንና ለእኛም የተገለጠውን የዘለዓለም ሕይወት እንነግራችኋለን። ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተም እንነግራችኋለን። አንድነታችንም ከአብና ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። ደስታችን ሙሉ እንዲሆን ይህን እንጽፍላችኋለን። ከእርሱ የሰማነውና ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት “እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም” የሚል ነው። ስለዚህ “ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት አለን” እያልን በጨለማ የምንኖር ከሆንን እንዋሻለን፤ በቃላችንም ሆነ በሥራችን እውነት የለም ማለት ነው። ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ እኛም በብርሃን ብንኖር እርስ በርሳችን አንድነት ይኖረናል። ደግሞም የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናታልላለን። እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። ኃጢአታችንን ለእግዚአብሔር ብንናዘዝ እርሱ ታማኝና ጻድቅ ስለ ሆነ ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር ይልልናል፤ ከበደላችንም ሁሉ ያነጻናል። ኃጢአት አልሠራንም ብንል እግዚአብሔርን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።