ይህም፦ “ ‘በተለያዩ ቋንቋዎች በሚናገሩ ሰዎችና በባዕድ ሰዎች አፍ ለዚህ ሕዝብ እናገራለሁ፤ ይህም ሆኖ አይሰሙኝም’ ይላል ጌታ እግዚአብሔር” ተብሎ በሕግ ተጽፎአል። ስለዚህ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገር ምልክት የሚሆነው ለማያምኑ ሰዎች ነው እንጂ ለሚያምኑ ሰዎች አይደለም፤ የትንቢት ቃል መናገር ግን ምልክት የሚሆነው ለሚያምኑት ሰዎች እንጂ ለማያምኑ ሰዎች አይደለም። ክርስቲያኖች በሚሰበሰቡበት ጊዜ እያንዳንዱ ክርስቲያን በተለያዩ ቋንቋዎች ቢናገርና የማያውቁ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢመጡ ተናጋሪዎችን “እነዚህ ሰዎች አብደዋል” አይሉምን? ነገር ግን እያንዳንዱ የትንቢት ቃል ቢናገርና የማያምን ወይም የማያውቅ ሰው ቢመጣ በሚሰማው ቃል ሁሉ ይወቀሳል፤ እንዲሁም በሚሰማው ቃል ሁሉ ይፈረድበታል። በልቡ የተሰወረው ነገር ይገለጣል፤ በግንባሩም ተደፍቶ “በእርግጥ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ነው!” በማለት ለእግዚአብሔር ይሰግዳል። ወንድሞች ሆይ! እንግዲህ ምን ማድረግ ይገባል? ለጸሎት በምትሰበሰቡበት ጊዜ ከእናንተ አንዱ የመዘመር ስጦታ አለው፤ ሌላው የማስተማር ስጦታ አለው፤ አንዱ ስውር የሆነውን ነገር የመግለጥ ስጦታ አለው፤ አንዱ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ስጦታ አለው፤ ሌላው የመተርጐም ስጦታ አለው። ታዲያ፥ ይህ ሁሉ ስጦታ ክርስቲያኖችን የሚያንጽ መሆን አለበት። በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ቢኖሩ ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በየተራ ይናገሩ፤ እነርሱ የሚናገሩትንም ሌላ ሰው ይተርጒም። የሚተረጒም ሰው ከሌለ ግን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩት በስብሰባ ላይ ዝም ይበሉ፤ ለራሳቸውና ለእግዚአብሔር ብቻ ይናገሩ። ትንቢት የሚናገሩ ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ፤ ሌሎቹ ግን የተነገረውን አዳምጠው በጥንቃቄ ያመዛዝኑ። በስብሰባ ላይ ለሚገኝ ሌላ ሰው አንዳች ራእይ ቢገለጥለት፤ የመጀመሪያው ተናጋሪ ዝም ይበል። እያንዳንዱ እንዲማርና እንዲጽናና ሁላችሁም በየተራ የእግዚአብሔርን መልእክት መናገር ትችላላችሁ። የነቢያት የትንቢት መንፈስ ለነቢያት ይታዘዛል። በእግዚአብሔር ሕዝብ አብያተ ክርስቲያን ሁሉ ዘንድ እንደሚደረገው እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም። ሴቶች በጸሎት ስብሰባ ጊዜ ዝም ይበሉ፤ ሕግ እንደሚያዘው እንዲታዘዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውም። አንዳንድ ነገርን ማወቅ ቢፈልጉ ባሎቻቸውን በቤታቸው ይጠይቁ፤ በጸሎት ስብሰባ ጊዜ ሴት እንድትናገር ተገቢ አይደለም። ለመሆኑ የእግዚአብሔር ቃል የመጣው ከእናንተ ነው? ወይስ የእግዚአብሔር ቃል የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነው? እኔ ነቢይ ነኝ ወይም እኔ መንፈሳዊ ስጦታ አለኝ የሚል ሰው ቢኖር ይህ የጻፍኩላችሁ የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ። ይህን የማያውቅ ቢኖር እርሱም አይታወቅም። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፤ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገርንም አትከልክሉ። ነገር ግን ሁሉ ነገር በአግባብና በሥነ ሥርዓት ይሁን።
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14:21-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች