እንግዲህ ወዳጆቼ ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ራቁ። ይህንንም የምላችሁ አስተዋዮች በመሆናችሁ ነው፤ ስለዚህ እኔ የምናገረውን እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። እኛ እግዚአብሔርን አመስግነን የምንካፈለው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰው ኅብስት ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? ኅብስቱ አንድ በመሆኑ እኛም ከዚህ ከአንዱ ኅብስት የምንካፈል ስለ ሆንን ምንም እንኳ ብዙዎች ብንሆን አንድ አካል ነን። እስቲ የእስራኤል ሕዝብ ያደረጉትን ተመልከቱ፤ የሚቀርበውን መሥዋዕት የሚበሉት ከመሠዊያው ጋር ኅብረት አልነበራቸውምን? ታዲያ ይህን ስል ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ የሚረባ ነገር ነው ማለቴ ነውን? ወይስ ጣዖት የሚረባ ነገር ነው ማለቴ ነውን? አይደለም! አሕዛብ መሥዋዕት የሚያቀርቡት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ስለዚህ እናንተ ከአጋንንት ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አልፈልግም፤ የጌታን ጽዋ እየጠጣችሁ ደግሞ የአጋንንትን ጽዋ መጠጣት አትችሉም፤ የጌታ ማእድ ተካፋዮች ሆናችሁ ደግሞ የአጋንንትን ማእድ ተካፋይ መሆን አትችሉም፤ ታዲያ ይህን በማድረግ ጌታን እናስቀናውን? እኛ ከእርሱ ይበልጥ እንበረታለንን? ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ ነገር ጠቃሚ አይደለም፤ ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ ነገር የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ ሰው የሌሎችንም ጥቅም ያስብ እንጂ የራሱን ጥቅም ብቻ አይፈልግ። ከኅሊናችሁ የሚነሣውን ጥርጣሬ አስወግዳችሁ ማንኛውንም በገበያ የሚሸጠውን ሥጋ ሳታመነቱ ብሉ። “ምድርና በእርስዋም ያለው ሁሉ የጌታ ነው።” ክርስቲያን ያልሆነ ሰው ቢጋብዛችሁና ግብዣውንም ብትቀበሉ የሚቀርብላችሁን ማንኛውንም ምግብ ከኅሊናችሁ የሚነሣውን ጥርጣሬ አስወግዳችሁ ሳታመነቱ ብሉ። ነገር ግን አንድ ሰው “ይህ ሥጋ ለጣዖት የተሠዋ ነው” ቢላችሁ ይህን በነገራችሁ ሰው ምክንያትና በኅሊናም ምክንያት ሥጋውን አትብሉ። ኅሊናም ስላችሁ የሰውዬውን ኅሊና ማለቴ ነው እንጂ የእናንተን ኅሊና ማለቴ አይደለም፤ ታዲያ በሌላው ሰው ኅሊና ምክንያት በእኔ ነጻነት ላይ የሚፈረደው ለምንድን ነው? እኔ እግዚአብሔርን እያመሰገንኩ ብበላ እግዚአብሔርን በማመሰግንበት ነገር ስለምን እወቀስበታለሁ? እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ ወይም ማናቸውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉ። አይሁድንም ቢሆን፥ አሕዛብንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔርንም ቤተ ክርስቲያን ቢሆን፥ ማንንም አታሰናክሉ። እኔ ሁሉም እንዲድኑ የሌሎችን ጥቅም እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ ሰውን ሁሉ በማደርገው ነገር ሁሉ እንደማስደስት እናንተም እንዲሁ አድርጉ።
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10:14-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች