አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 28

28
ዳዊት ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ የሰጠው መመሪያ
1ንጉሥ ዳዊት የእስራኤል ባለ ሥልጣኖች በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው እንዲሰበሰቡ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ስለዚህ የየነገዱ መሪዎች፥ የመንግሥቱን ሥራ የሚያካሂዱ ባለሥልጣኖች የሻአለቆችና የመቶ አለቆች፥ የንጉሡንና የወንዶች ልጆቹን ንብረትና የቀንድ ከብት ተቈጣጣሪዎች እንዲሁም የቤተ መንግሥት ባለሟሎች፥ ዝነኞችና ታዋቂ የሆኑ ጀግኖች ሰዎች በሙሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።
2ሁሉም በተሰበሰቡ ጊዜ ዳዊት ተነሥቶ፥ እንዲህ አለ፦ “ወገኖቼ ሆይ፥ አድምጡኝ፤ ለአምላካችን የእግር ማሳረፊያ ይሆን ዘንድ የተቀደሰው ታቦት የሚያርፍበት ቤት ለመሥራት ፈልጌ ነበር፤ ለቤተ መቅደሱም ሕንጻ ማሠሪያ የሚሆነውን ዕቃ ሁሉ አዘጋጅቼአለሁ፤ 3ነገር ግን እኔ በጦርነት ብዙ ደም በማፍሰሴ ቤተ መቅደሱን እንድሠራለት እግዚአብሔር አልፈቀደልኝም፤ 4የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፥ ይሁዳን በእስራኤል ላይ መሪ ነገድ አድርጎ መርጦታል፤ ከይሁዳም የእኔን ቤተሰብ፥ ከእኔም ቤተሰብ እኔን የእስራኤል ንጉሥ እንድሆን መረጠኝ፤ የእኔም ዘሮች ነገሥታት ሆነው እንደሚያስተዳድሩ ቃል ገብቶልኛል። 5ለእኔም ብዙ ወንዶች ልጆችን ሰጠኝ፤ ነገር ግን የሚቀጥለው የእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ የመረጠው ልጄን ሰሎሞንን ነው።”
6እግዚአብሔርም “ ‘ቤተ መቅደሴንና አደባባዮቼን የሚሠራልኝ ልጅህ ሰሎሞን ነው፤ እርሱ እንደ ልጄ ይሆናል፤ እኔም እንደ አባት እሆነዋለሁ’ ብሎኛል። 7‘እርሱ አሁን በሚያደርገው ዐይነት ዘወትር ሕጎቼንና ትእዛዞቼን በጥንቃቄ የሚፈጽም ከሆነ፥ መንግሥቱን ለዘለዓለም አጸናለታለሁ’ ብሎአል። #2ሳሙ. 7፥1-6፤ 1ዜ.መ. 17፥1-14።
8“አሁንም ሕዝቤ ሆይ፥ በእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆነው በዚህ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት አምላካችን እግዚአብሔር ያዘዘንን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ትፈጽሙ ዘንድ ዐደራ እላችኋለሁ፤ ይህን ብታደርጉ ይህችን መልካም ምድር ለዘለቄታው ርስታችሁ ታደርጋላችሁ፤ ወደፊት ለሚመጡትም ለልጅ ልጆቻችሁ ማስተላለፍ ትችላላችሁ።”
9ዳዊት ሰሎሞንንም እንዲህ አለው፤ “ልጄ ሆይ፥ የአባትህን አምላክ እንድታውቅ፥ በሙሉ ልብና በፈቃደኛ አእምሮ እንድታገለግለው ዐደራ እልሃለሁ፤ እርሱ ሐሳባችንንና ምኞታችንን ሁሉ ያውቃል፤ ወደ እርሱ ብትቀርብ እርሱም ወደ አንተ ይቀርባል፤ ብትተወው ግን እርሱም ለዘለዓለም ይተውሃል፤ 10ቤተ መቅደሱን ትሠራለት ዘንድ እግዚአብሔር አንተን እንደ መረጠህ አትዘንጋ፤ አሁንም በርትተህ በቈራጥነት ሥራው።”
11ዳዊት ለልጁ ለሰሎሞን የቤተ መቅደሱን የዕቃ ግምጃ ቤቶቹን፥ በደርቡና በምድር ቤቱ የሚገኙትን ክፍሎችና ኃጢአት የሚሰረይበትን የቅድስተ ቅዱሳኑን አሠራር የሚገልጥ ዕቅድ ሰጠው። 12ለአደባባዮቹና በዙሪያቸው ላሉት ክፍሎች፥ ለቤተ መቅደሱ ዕቃና ለእግዚአብሔር ለሚቀርቡ መባዎች የዕቃ ግምጃ ቤት በሐሳቡ የነበረውን ሁሉ የአሠራር ዕቅድ ጨምሮ ሰጠው። 13እንዲሁም ዳዊት ስለ ካህናትና ሌዋውያን የተለያየ የሥራ ድርሻ፥ በቤተ መቅደሱ ስለሚከናወኑት ተግባሮችና እግዚአብሔርን ለማምለክ አገልግሎት መጠቀሚያ ለሆኑት ዕቃዎች ለሚደረገው እንክብካቤ ዕቅድ ለሰሎሞን ሰጠው። 14ለተለያዩ የአገልግሎት ዐይነቶች መጠቀሚያ የሚሆኑትን ዕቃዎች መሥሪያ እንዲሆኑ የብሩንና የወርቁን መጠን በሚዛን ወሰነ። 15ለያንዳንዱ መቅረዝና መብራት የሚሆን ወርቅ፥ እንዲሁም ለመቅረዙና ለመብራቱ የሚሆን ብር መዝኖ ሰጠው። 16ለተቀደሰው ኅብስት ማስቀመጫ ለሚሆን ወርቁን፥ ለሌሎች ጠረጴዛዎች ማሠሪያ ብሩን መዝኖ ሰጠው። 17እንዲሁም ሹካዎችን፥ ድስቶችንና ማንቆርቆሪያዎችን ለመሥራት ምን ያኽል ንጹሕ ወርቅና ሳሕኖቹንም ለመሥራት የሚያስፈልገውን ብርና ወርቅ መዝኖ ሰጠ፤ 18እንዲሁም ዕጣን የሚታጠንበትን መሠዊያና ክንፎቻቸውን ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት በላይ የዘረጉት ኪሩቤል የሚቀመጡበት ሠረገላ የሚሠሩበት ምን ያኽል ንጹሕ ወርቅ እንደሚያስፈልግ መመሪያ ሰጠ፤ 19ቀጥሎም ንጉሥ ዳዊት “ይህ ሁሉ እግዚአብሔር ራሱ በሥራ ላይ እንዳውለው በሰጠኝ መመሪያ መሠረት በጽሑፍ የሰጠኝ ዕቅድ ነው” አለ።
20ንጉሥ ዳዊት ለልጁ ለሰሎሞንም እንዲህ አለ፤ “አይዞህ በርታ ሥራውንም በቶሎ ጀምር፤ ምንም ነገር አይግታህ፤ እኔ የማገለግለው እግዚአብሔር አምላክ ከአንተ ጋር ነው፤ ለቤተ መቅደሱ ሥራ ያለህን አገልግሎት እስክትፈጽም ድረስ ከአንተ አይለይም፤ አይተውህም፤ ከቶም አይጥልህም፤ 21በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለውን አገልግሎት እንዲፈጽሙ ካህናትና ሌዋውያን ተመድበዋል፤ ልዩ ልዩ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞች ይረዱሃል፤ ሕዝቡና መሪዎቻቸው ሁሉ ለአንተ ይታዘዛሉ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ