አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23

23
1ዳዊት በጣም በሸመገለ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው። #1ነገ. 1፥1-40።
የሌዋውያን አገልግሎት
2ንጉሥ ዳዊት የእስራኤልን አለቆች እንዲሁም ካህናትንና ሌዋውያንን በሙሉ በአንድነት ሰበሰበ፤ 3ዕድሜአቸው ሠላሳና ከዚያም በላይ የሆኑትን ሌዋውያን ወንዶችን ቈጠረ፤ ጠቅላላ ድምራቸውም ሠላሳ ስምንት ሺህ ሆነ፤ 4ንጉሡ ከእነርሱ ኻያ አራት ሺህ የሚሆኑትን የእግዚአብሔርን የቤተ መቅደስ ሥራ እንዲያሠሩ መደባቸው፤ ስድስት ሺህ የሚሆኑትን ባለሥልጣኖችና ዳኞች ሆነው እንዲሠሩ መደባቸው። 5አራት ሺህ የሚሆኑ ደግሞ ለዘብ ጥበቃ ተመደቡ፤ ሌሎች አራት ሺህ ደግሞ ንጉሡ በሚሰጣቸው የሙዚቃ መሣሪያ እግዚአብሔርን በዝማሬ ለማመስገን ተመደቡ።
6ዳዊት ሌዋውያንን በየጐሣቸው ክፍል መሠረት በሦስት ቦታ መደባቸው፤ እነርሱም ጌርሾን፥ ቀዓትና መራሪ ተብለው የሚጠሩት ናቸው።
7ጌርሾን ላዕዳንና ሺምዒ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ 8ላዕዳንም ይሒኤል፥ ዜታምና ኢዮኤል ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ 9ሺምዒም ሸሎሞት፥ ሐዚኤልና ሃራን ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፥ እነዚህ ሁሉ የላዕዳን ዘሮች ለሆኑት ጐሣዎች አለቆች ነበሩ፤ 10-11ሺምዒም በዕድሜአቸው ተራ ያሐት፥ ዚዛ፥ ይዑሽና በሪያ ተብለው የሚጠሩ አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ያሖት የመጀመሪያው፥ ዚዛ ሁለተኛው ነበሩ፤ ይዑሽና በሪያ ብዙ ልጆች ስላልነበሩአቸው እንደ አንድ ጐሣ ይቈጠሩ ነበር።
12ቀዓትም ዓምራም፥ ዩጺሃር፥ ኬብሮንና ዑዚኤል ተብለው የሚጠሩ አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ 13የቀዓት የበኲር ልጅ ዓምራም፥ የአሮንና የሙሴ አባት ነበር፤ አሮንና ዘሮቹ ለዘለቄታው ለንዋያተ ቅድሳት ኀላፊዎች እንዲሆኑ፥ እግዚአብሔርን በማምለክ ሥነ ሥርዓት ላይ ዕጣን እንዲያጥኑ፥ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉና በስሙም ሕዝቡን እንዲባርኩ ተለይተው ነበር፤ #ዘፀ. 28፥1። 14የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ልጆች ቊጥራቸው ከሌዋውያን ጋር ነበር። 15ሙሴም ጌርሾምና ኤሊዔዘር ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ 16ከጌርሾም ወንዶች ልጆች መካከል መሪው ሸቡኤል ነበር፤ 17ኤሊዔዘርም ረሐብያ ተብሎ የሚጠራ አንድ ወንድ ልጅ ብቻ ነበረው፤ ረሐብያ ግን ብዙ ዘሮች ነበሩት።
18የቀዓት ሁለተኛ ልጅ ይጽሐር የጐሣው አለቃ የነበረ ሸሎሚት ተብሎ የሚጠራ አንድ ወንድ ልጅ ነበረው፤ 19የኬብሮንም ልጆች አለቃ ይሪያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው ያሕዚኤልና አራተኛው ይቃምዓም ተብለው የሚጠሩ አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት። 20አራተኛ የዑዚኤልም ልጆች አለቃ ሚካ፥ ሁለተኛው ዩሺያ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት።
21መራሪም ማሕሊና ሙሺ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ማሕሊም አልዓዛርና ቂሽ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት። 22አልዓዛር ግን ከሴቶች በቀር አንድም ወንድ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ የእርሱ ሴቶች ልጆች የአጐታቸውን የቂሽን ወንዶች ልጆች አገቡ፤ 23የመራሪ ሁለተኛ ልጅ ሙሺም ማሕሊ ዔዴርና ይሬሞት ተብለው የሚጠሩ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት።
24እንግዲህ እነዚህ ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተሰባቸው የተዘረዘሩት የሌዊ ዘሮች ሲሆኑ፥ እያንዳንዳቸው በየስማቸው ተጠቅሰዋል። ኻያ ዓመት የሞላው ወይም ከዚያ በላይ የሆነው እያንዳንዱ የሌዊ ዘር በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ባለው ሥራ ድርሻ ነበረው።
25ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሰላምን ሰጥቶአል፤ ከዚህም በላይ እርሱ ራሱ በኢየሩሳሌም ለዘለዓለም ይኖራል፤ 26ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ እግዚአብሔር የሚመለክበትን ድንኳንና ለአምልኮ ሥነ ሥርዓት መገልገያ የሆኑትን ዕቃዎች ሌዋውያን መሸከም አይኖርባቸውም።” #ዘዳ. 10፥8። 27ዳዊት ለመጨረሻ ጊዜ በሰጠው መመሪያ መሠረት ሌዋውያን ሁሉ ኻያ ዓመት የሞላቸውና ከዚያ በላይ የሆኑ ተመዘገቡ፤ 28ኀላፊነታቸውም የአሮን ልጆች በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በሚያከናውኑት ተግባር መርዳት፥ የአደባባዩንና የክፍሎቹን እንክብካቤ መጠበቅ፥ ንዋያተ ቅድሳትን ማንጻት፥ እንዲሁም አጠቃላይ የሆነውን የቤተ መቅደሱን አገልግሎት ማከናወን ነው። 29ለእግዚአብሔር መባ ሆኖ ለሚቀርበው ኅብስትና ዱቄት፥ ያለ እርሾ ለሚጋገረው ቂጣና በወይራ ዘይት ለሚለወሰው ዱቄት ኀላፊዎች ሲሆኑ፥ ለቤተ መቅደስ መባ ሆኖ የሚቀርበውን ሁሉ የሚመዝኑና የሚለኩ እነርሱ ነበሩ፤ 30-31ዘወትር ጠዋትና ማታ፥ እንዲሁም ለእግዚአብሔር መባ ሆኖ የሚቀርበው ነገር በሚቃጠልበት በየሰንበቱ፥ በየወሩ መባቻና በሌሎችም በዓላት እግዚአብሔርን ማመስገንና ማክበር የእነርሱ ተግባር ነበር፤ በየጊዜው ይህን አገልግሎት የሚፈጽሙ ሌዋውያን ቊጥራቸው ምን ያኽል መሆን እንደሚገባው ደንቦች ነበሩ፤ ሌዋውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ በሚደረገው ሥነ ሥርዓት ለሁልጊዜ ተመድበዋል። 32እንዲሁም እግዚአብሔር የሚመለክበትን ድንኳንና ቤተ መቅደሱን የመንከባከብ ኀላፊነት የእነርሱ ነበር፤ በተጨማሪም በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚፈጸመው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ዘመዶቻቸውን የአሮን ዘሮች የሆኑ ካህናትን ይረዱ ነበር። #ዘኍ. 3፥5-9።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ