አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 19

19
ዳዊት ዐሞናውያንንና ሶርያውያንን ድል ማድረጉ
(2ሳሙ. 10፥1-19)
1ከጥቂት ጊዜ በኋላ የዐሞን ንጉሥ ናዖስ ሞተ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ሐኑን ነገሠ፤ 2ንጉሥ ዳዊትም “አባቱ ናዖስ ለእኔ እንዳደረገልኝ ሁሉ፥ እኔም ለልጁ ለሐኑን ታማኝ ወዳጅ በመሆን ወሮታውን እከፍላለሁ” አለ፤ ስለዚህም ዳዊት የሐዘን ተካፋይነቱን ለመግለጥ መልእክተኞች ላከ።
መልእክተኞቹም ሊያጽናኑት ወደ ዐሞን ምድር በደረሱ ጊዜ፥ 3ዐሞናውያን ባለሥልጣኖች ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ዳዊት እነዚህን ሰዎች የላከው አባትህን በማክበር የሐዘንህ ተካፋይ ለመሆን ይመስልሃልን? ከቶ እንዳይመስልህ! እርሱ እነዚህን መልእክተኞች የላከው ምድሪቱን ወሮ መያዝ ይችል ዘንድ እንዲሰልሉለት ነው።”
4ስለዚህ ሐኑን የዳዊትን መልእክተኞች ይዞ ጢማቸውን ላጨ፤ ኀፍረተ ሥጋቸው እስኪታይ ድረስ ከወገባቸው በታች ያለውን ልብስ ቈረጠና ወደ አገራቸው ሰደዳቸው፤ 5እነርሱም ወደ ቤታቸው ለመመለስ አፈሩ፤ ዳዊት ስለ ሆነው ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ መልእክተኞች ልኮ በኢያሪኮ እንዲቈዩና ጢማቸው እስከሚያድግ ድረስ እንዳይመለሱ ነገራቸው።
6ዐሞናውያን በገዛ እጃቸው ዳዊትን ጠላት እንዳደረጉት ተገነዘቡ፤ ስለዚህም ሠላሳ አራት ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር ከፍለው ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ከላይኛው መስጴጦምያና የሶርያ ግዛቶች ከሆኑት ከማዕካና ከጾባ ተከራዩ፤ 7የተከራዩአቸው ሠላሳ ሁለት ሺህ ሠረገሎችና የንጉሥ ማዕካ ሠራዊት መጥተው በሜዳባ አጠገብ ሰፈሩ፤ ዐሞናውያንም ከየከተሞቻቸው ወጥተው ለጦርነት ተዘጋጁ።
8ዳዊት ስለዚህ ጉዳይ ሰምቶ ከመላው ሠራዊት ጋር ኢዮአብን በእነርሱ ላይ አዘመተ፤ 9ዐሞናውያንም ተሰልፈው መጥተው የእነርሱ ዋና ከተማ በሆነችው በራባ መግቢያ በር አጠገብ ስፍራቸውን ያዙ፤ እነርሱን ሊረዱ የመጡ ነገሥታትም ገላጣማ በሆነው ገጠር ስፍራቸውን ያዙ።
10ኢዮአብ የጠላት ሠራዊት ከፊትና ከኋላ በኩል አደጋ እንደሚጥልበት ተመለከተ፤ ስለዚህ ከእስራኤል ወታደሮች ጀግኖች የሆኑትን መርጦ በሶርያውያን ሠራዊት ፊት ለፊት አቆማቸው። 11ከሠራዊቱ ቀሪውን ክፍል በወንድሙ በአቢሳ ትእዛዝ ሥር አደረገ፤ አቢሳም እነርሱን በዐሞናውያን ፊት ለፊት አሰለፋቸው።
12ኢዮአብም አቢሳን እንዲህ አለው፤ “ሶርያውያን ድል ሊያደርጉኝ መቃረባቸውን በምታይበት ጊዜ መጥተህ እርዳኝ፤ እኔም ዐሞናውያን አንተን ድል ሊያደርጉህ በሚቃረቡበት ጊዜ መጥቼ እረዳሃለሁ፤ 13እንግዲህ አይዞህ በርታ! ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተማዎች ስንል በርትተን እንዋጋ፤ ለዚህም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን።”
14ኢዮአብና ሠራዊቱ አደጋ ለመጣል ወደፊት በገሠገሡ ጊዜ ሶርያውያን ሸሹ፤ 15ዐሞናውያንም የሶርያውያንን መሸሽ ባዩ ጊዜ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማይቱ አፈገፈጉ፤ ከዚህ በኋላ ኢዮአብ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
16ሶርያውያን በእስራኤላውያን ድል እንደ ተመቱ በተገነዘቡ ጊዜ ከኤፍራጥስ በስተ ምሥራቅ በኩል ካሉት የሶርያ ግዛቶች ሠራዊት አስመጥተው በሾባክ አዛዥነት ሥር አደረጉአቸው፤ ሾባክ የጾባ ንጉሥ የሀዳድዔዜር የጦር አዛዥ ነበር፤ 17ዳዊት ስለዚህ ነገር በሰማ ጊዜ የእስራኤላውያንን የጦር ኀይል ሰበሰበ፤ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ የውጊያ መስመሩን ያዘ፤ ሶርያውያንም እንደዚሁ ቦታቸውን ይዘው ከዳዊት ጋር ጦርነት ገጠሙ። 18እስራኤላውያንም ሶርያውያንን ወደ ኋላ መልሰው አባረሩአቸው፤ ዳዊትና ሠራዊቱ ሰባት ሺህ ሠረገላ ነጂዎችን፥ አርባ ሺህ እግረኛ ወታደሮችን ገደሉ፤ እንዲሁም ሾባክ ተብሎ የሚጠራውን የሶርያውያንን የጦር አዛዥ ገደሉ፤ 19በሀዳድዔዜር ሥልጣን ሥር የነበሩት ነገሥታት በእስራኤል ድል እንደ ተመቱ በተገነዘቡ ጊዜ ከዳዊት ጋር የሰላም ስምምነት አድርገው የእርሱ ገባሮች ሆኑ፤ ከዚያን በኋላም ሶርያውያን ዐሞናውያንን ለመርዳት ፈቃደኞች አልሆኑም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ