ሶፎንያስ 2

2
ይሁዳና ኢየሩሳሌም ከሌሎች ሕዝቦች ጋራ ተፈረደባቸው
ይሁዳ ለንስሓ ተጠራ
1እናንተ ዕፍረት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፤
በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ተከማቹም፤
2የተወሰነው ጊዜ ሳይደርስ፣
ቀኑ እንደ ገለባ ሳይጠራርጋችሁ፣
እግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ በእናንተ ላይ ሳይመጣ፣
እግዚአብሔር የመዓት ቀን
ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ።
3እናንተ የምድር ትሑታን ሁሉ፣
ትእዛዙን የምትፈጽሙ፣ እግዚአብሔርን እሹ፤
ጽድቅንና ትሕትናን ፈልጉ፤
እግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣
ትሰወሩ ይሆናል።
በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ጥፋት
4ጋዛ ባድማ ትሆናለች፤
አስቀሎናም ፈራርሳ ትቀራለች፤
አዛጦን በቀትር ባዶ ትሆናለች፤
አቃሮንም ትነቀላለች።
5እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ፣
የከሊታውያን ሰዎች ሆይ፤ ወዮላችሁ!
የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፤
በአንቺ ላይ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤
“ፍጹም አጠፋሻለሁ፤
ከነዋሪዎችሽም የሚተርፍ የለም።”
6የቀርጤስ#2፥6 የዕብራይስጡ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። ሰዎች የሚኖሩበት በባሕሩ
ዳር ያለው ምድር፣
የእረኞች መኖሪያና የበጎች በረት ይሆናል፤
7ይህም ለይሁዳ ቤት ትሩፍ ይሰጣል፤
እነርሱም በዚያ መሰማሪያ ያገኛሉ።
በአስቀሎና ቤቶች ውስጥም
በምሽት ይተኛሉ፤
አምላካቸው እግዚአብሔር ይጐበኛቸዋል፤
ምርኳቸውንም ይመልስላቸዋል።
በሞዓብና በአሞን ላይ የተነገረ ጥፋት
8“የሞዓብን ስድብ፣
የአሞናውያንንም ፌዝ ሰምቻለሁ፤
ሕዝቤን ሰድበዋል፤
በምድራቸውም ላይ ዝተዋል።”
9ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“በሕያውነቴ እምላለሁ፤
ሞዓብ እንደ ሰዶም፣
አሞናውያን እንደ ገሞራ፣
ዐረም እንደ ዋጠው ቦታና እንደ ጨው
ጕድጓድ ለዘላለም ጠፍ ይሆናሉ።
ከሕዝቤ የቀሩት ይዘርፏቸዋል፤
ከወገኔ የተረፉትም ምድራቸውን
ይወርሳሉ።”
10ከትዕቢታቸው የተነሣ የሚደርስባቸው ይህ ነው፤
የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕዝብ
ሰድበው ዘብተውበታልና፣
11 እግዚአብሔር የምድሪቱን አማልክት
ሁሉ በሚደመስስበት ጊዜ፣
በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፤
በየባሕሩ ጠረፍ የሚኖሩ ሕዝቦች፣
እያንዳንዳቸው በያሉበት ሆነው ለርሱ ይሰግዳሉ።
በኢትዮጵያ ላይ የተነገረ ጥፋት
12“ኢትዮጵያውያን#2፥12 ይህ ከአባይ ወንዝ በስተሰሜን ያለ አካባቢን የሚያመላክት ነው። ሆይ፤ እናንተም፣
በሰይፌ ትገደላላችሁ።”
በአሦር ላይ የተነገረ ጥፋት
13እጁን በሰሜን ላይ ይዘረጋል፤
አሦርንም ያጠፋል፤
ነነዌን ፍጹም ባድማ፣
እንደ ምድረ በዳም ደረቅ ያደርጋታል።
14የበግና የከብት መንጋዎች፣
የፍጥረት ዐይነት ሁሉ በውስጧ ይመሰጋሉ፤
ጕጕትና ጃርት፣
በግንቦቿ ላይ ያድራሉ።
ጩኸታቸው በየመስኮቱ ያስተጋባል፤
ፍርስራሽ በየደጃፉ ይከመራል፤
ከዝግባ የተሠሩ ተሸካሚዎችም ይገለጣሉ።
15ያለ ሥጋት የኖረች፣
ደስተኛዪቱ ከተማ ይህች ናት፤
እርሷም በልቧ፣
“እኔ ብቻ ነኝ! ከእኔ በቀር ማንም የለም” ያለች፣
ታዲያ እንዴት የዱር አራዊት የሚመሰጉባት፣
ባድማ ሆና ቀረች?
በአጠገቧ የሚያልፉ ሁሉ፣
ያፌዙባታል፤ እጃቸውንም በንቀት ያወዛውዙባታል።

Currently Selected:

ሶፎንያስ 2: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ