ዘካርያስ 8:14-23

ዘካርያስ 8:14-23 NASV

የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ ባስቈጡኝ ጊዜ ያለ አንዳች ሐዘኔታ ጥፋት ላመጣባችሁ እንደ ወሰንሁ፣” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤ “አሁን ደግሞ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ መልካም ነገርን ላደርግ ወስኛለሁ፤ አትፍሩ። ልታደርጓቸው የሚገባችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፤ እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በአደባባያችሁም እውነትንና ትክክለኛ ፍርድን አስፍኑ፤ በባልንጀራችሁ ላይ ክፋትን በልባችሁ አታውጠንጥኑ፤ በሐሰት መማልን አትውደዱ፤ እነዚህን ሁሉ እጸየፋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። እንደ ገናም የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የአራተኛው፣ የአምስተኛው፣ የሰባተኛውና የዐሥረኛው ወር ጾሞች ለይሁዳ ቤት የደስታ፣ የተድላና የሐሤት በዓላት ይሆናሉ፤ ስለዚህ እውነትንና ሰላምን ውደዱ።” የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ብዙ ሕዝቦችና የብዙ ከተሞች ነዋሪዎች ገና ይመጣሉ፤ የአንዲቱ ከተማ ነዋሪዎችም፣ ‘እግዚአብሔርን ለመለመን የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ለመፈለግ፣ ኑ፤ በፍጥነት እንሂድ፤ እኔም ራሴ እሄዳለሁ’ እያሉ ወደ ሌላዪቱ ከተማ ይሄዳሉ። ብዙ ሕዝብና ኀያላን መንግሥታትም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ለመፈለግና ለመለመን ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ።” የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በእነዚያም ቀናት ከየወገኑና ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ እንዳለ ሰምተናልና ዐብረን እንሂድ’ ” ይሉታል።