ሮሜ 9:19-33
ሮሜ 9:19-33 NASV
ከእናንተ አንዱ፣ “ታዲያ እንደዚህ ከሆነ እግዚአብሔር እስከ አሁን ለምን ይወቅሠናል? ምክንያቱም ፈቃዱን ሊቋቋም የሚችል ማን አለ?” ይለኝ ይሆናል። ነገር ግን ለእግዚአብሔር መልስ የምትሰጥ አንተ ማን ነህ? “ሥራ ሠሪውን፣ ‘ለምን እንዲህ ሠራኸኝ?’ ይለዋልን?” ሸክላ ሠሪ፣ ከሚሠራው ጭቃ፣ አንዳንዱን ሸክላ ለከበረ፣ ሌሎቹን ደግሞ ለተራ አገልግሎት የማድረግ መብት የለውምን? እግዚአብሔር ቍጣውን ለማሳየት፣ ኀይሉንም ለማሳወቅ ፈልጎ የቍጣው መግለጫ የሆኑትን፣ ለጥፋትም የተዘጋጁትን እጅግ ታግሦ ቢሆንሳ? አስቀድሞ ለክብር ላዘጋጃቸው፣ የምሕረቱም መግለጫዎች ለሆኑት፣ የክብሩ ባለጠግነት እንዲታወቅ ይህን አድርጎ እንደሆነስ? የጠራው ከአይሁድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብ ወገን የሆንነውን እኛን እንኳ ሳይቀር አይደለምን? በሆሴዕ እንዲህ እንደሚል፤ “ሕዝቤ ያልሆኑትን፣ ‘ሕዝቤ’ ብዬ፣ ያልተወደደችውንም፣ ‘የተወደደች’ ብዬ እጠራለሁ።” ደግሞም፣ “ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ ተብሎ በተነገራቸው በዚያ ቦታ፣ ‘የሕያው እግዚአብሔር ልጆች’ ተብለው ይጠራሉ።” ኢሳይያስም ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ይጮኻል፤ “የእስራኤል ልጆች ቍጥር በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ቢሆንም፣ ትሩፉ ብቻ ይድናል። ጌታ ፍርዱን በምድር ላይ፣ በፍጥነትና ለመጨረሻ ጊዜ ይፈጽማልና።” ይኸውም ቀደም ሲል ኢሳይያስ እንደ ተናገረው ነው፤ “የሰራዊት ጌታ፣ ዘር ባያስቀርልን ኖሮ፣ እንደ ሰዶም በሆንን፣ ገሞራንም በመሰልን ነበር።” እንግዲህ ምን እንበል? በእምነት የሆነውን ጽድቅ፣ ለጽድቅ ያልደከሙት አሕዛብ አገኙት፤ ነገር ግን የጽድቅን ሕግ የተከታተሉት እስራኤል አላገኙትም። ይህ ለምን ሆነ? በእምነት ሳይሆን በሥራ እንደ ሆነ አድርገው በመቍጠር ስለ ተከታተሉት ነው፤ እነርሱም፣ “በማሰናከያው ድንጋይ” ተሰናከሉ። ይህም፣ “እነሆ፤ የሚያደናቅፍ ድንጋይ፣ የሚጥልም ዐለት፣ በጽዮን አስቀምጣለሁ፤ በርሱም የሚያምን አያፍርም” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።

