ዘሌዋውያን 4
4
የኀጢአት መሥዋዕት
1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ 2“ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፤
3“ ‘የተቀባውም ካህን በሕዝቡ ላይ በደል የሚያስከትል ኀጢአት ቢሠራ፣ ስለ ሠራው ኀጢአት እንከን የሌለበት አንድ ወይፈን ለእግዚአብሔር የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። 4ወይፈኑን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫን፤ በእግዚአብሔርም ፊት ይረደው። 5የተቀባው ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ፤ 6ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ ከመቅደሱ መጋረጃ ትይዩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። 7ካህኑ ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለውንና ሽታው ጣፋጭ የሆነ ዕጣን የሚታጠንበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ። የተረፈውን የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። 8ለኀጢአት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ይኸውም፦ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብና ከሆድ ዕቃው ጋራ የተያያዘውን ሥብ፣ 9ሁለቱንም ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጕበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋራ ዐብሮ አውጥቶ ያቅርብ፤ 10ለኅብረት መሥዋዕት#4፥10 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል፤ እንዲሁም 4፥26፣31፣35 ይመ፤ ከሚቀርበው ወይፈን#4፥10 የዕብራይስጡ ቃል ተባዕትንና እንስትን ሊያጠቃልል ይችላል። እንዳወጣ ሁሉ ሥቡን ያውጣ፤ ካህኑም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለው። 11ነገር ግን የወይፈኑን ቈዳና ሥጋውን ሁሉ፣ ጭንቅላቱንና እግሮቹን፣ ሆድ ዕቃውንና ፈርሱን፣ 12የወይፈኑን ብልት ሁሉ ከሰፈር ውጭ ዐመድ ወደሚፈስስበት በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነው ስፍራ ይውሰደው፤ በተቈለለው ዐመድ ላይ ዕንጨት አንድዶ ያቃጥለው።
13“ ‘መላው የእስራኤል ሕዝብ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አታድርጉ ብሎ እግዚአብሔር ካዘዘውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ ይህ ሕዝብ ጥፋቱ ባይታወቀውም በደለኛ ነው። 14የሕዝቡ ጉባኤ ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን በመገናኛው ድንኳን ፊት ያቅርብ። 15የሕዝቡም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ፊት እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫኑ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር ፊት ይታረድ። 16የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ። 17ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ በመጋረጃው ትይዩ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። 18ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለውን የመሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። 19ከወይፈኑም ሥቡን ሁሉ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ 20ለኀጢአት መሥዋዕት ባቀረበው ወይፈን ላይ እንዳደረገው ሁሉ፣ በዚህኛውም ወይፈን ያድርግ፤ በዚህም መሠረት ካህኑ ስለ ሕዝቡ ያስተሰርያል፤ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። 21ወይፈኑንም ከሰፈር ውጭ ያውጣው፤ የመጀመሪያውን ወይፈን እንዳቃጠለው ሁሉ ይህኛውንም ያቃጥል፤ ይህም ስለ ሕዝቡ የሚቀርብ የኀጢአት መሥዋዕት ነው።
22“ ‘አንድ የሕዝብ መሪ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አምላኩም እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዞች አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ እርሱ በደለኛ ነው። 23ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ እንከን የሌለበትን ተባዕት ፍየል የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። 24እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበትም ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። 25ካህኑም ከመሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍስሰው። 26የኅብረት መሥዋዕቱን እንዳቃጠለ ሁሉ ሥቡንም በሙሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።
27“ ‘ከሕዝቡ መካከል አንዱ ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዞች አንዱን ተላልፎ ቢገኝ እርሱ በደለኛ ነው። 28ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ፍየል ስለ ፈጸመው ኀጢአት የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። 29እጁን ለኀጢአት መሥዋዕት በቀረበችው ፍየል ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራም ይረዳት። 30ካህኑ በጣቱ ከደሟ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍስሰው። 31ሥቡን ከኅብረት መሥዋዕት በወጣበት አኳኋን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ካህኑም ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።
32“ ‘ስለ ኀጢአት መሥዋዕት የበግ ጠቦት የሚያቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ያቅርብ። 33እጁን በጠቦቷ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራም የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረዳት። 34ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። 35ሥቡ ከኅብረት መሥዋዕት ጠቦት በወጣበት አኳኋን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በእሳት በሚቀርበው መሥዋዕት ላይ ያቃጥለው። በዚህ መሠረት ሰውየው የሠራውን ኀጢአት ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.