ዘሌዋውያን 22
22
1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“እስራኤላውያን ቀድሰው ለእኔ የለዩትን ቅዱስ መሥዋዕት በአክብሮት ባለመያዝ፣ ቅዱስ ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
3“እንዲህም በላቸው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ከዘርህ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው፣ እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ለይተው ወዳቀረቡት ቅዱስ መሥዋዕት ቢቀርብ ያ ሰው ከፊቴ ይወገድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
4“ ‘ከአሮን ዘር ተላላፊ የቈዳ በሽታ#22፥4 በትውፊት ለምጽ ይባላል፤ የዕብራይስጡ ቃል ለምጽ ብቻ ሳይሆን ከቈዳ ጋራ የተያያዘ በሽታን ያመለክታል ያለበት ወይም ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ማንኛውም ሰው እስኪነጻ ድረስ ቅዱሱን መሥዋዕት አይብላ፤ እንዲሁም በአስከሬን የረከሰውን ነገር ወይም የዘር ፈሳሽ ያለበትን ሰው ቢነካ፣ 5ወይም በደረቱ የሚሳብ የሚያረክስ ነገርን ወይም የሚያረክስ ማንኛውንም ሰው ቢነካ፣ የቱንም ዐይነት ርኩሰት ቢሆን፣ 6እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ነገር የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ሰውነቱንም በውሃ ካልታጠበ፣ የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ። 7ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ የተቀደሰውን መሥዋዕት መብላት ይችላል፤ ምግቡ ነውና። 8እንዳይረክስ ማንኛውንም ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የዘነጠለውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
9“ ‘ካህናት ትእዛዞቼን በመናቅ በደለኛ እንዳይሆኑና እንዳይሞቱ ይጠብቋቸው፤ የምቀድሳቸው#22፥9 ወይም ቅዱስ አድርጌ የምለያቸው፤ እንዲሁም 16 ይመ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
10“ ‘ከካህን ቤተ ሰብ በቀር የካህኑ እንግዳም ሆነ ቅጥር ሠራተኛ የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ። 11ነገር ግን ካህኑ በገንዘብ የገዛው ወይም በቤቱ የተወለደ ባሪያ ቢኖረው፣ ያ ባሪያ ከካህኑ ድርሻ መብላት ይችላል። 12የካህን ልጅ፣ ካህን ያልሆነ ሌላ ሰው ካገባች፣ ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አትችልም። 13ይሁን እንጂ የካህኑ ልጅ ባሏ ቢሞት ወይም ብትፋታ፣ ልጆችም ባይኖሯትና እንደ ልጅነት ጊዜዋ በአባቷ ቤት ለመኖር ብትመለስ፣ ከአባቷ ድርሻ መብላት ትችላለች፤ ያልተፈቀደለት ሰው ግን ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አይችልም።
14“ ‘ማንኛውም ሰው ባለማወቅ የተቀደሰውን መሥዋዕት ቢበላ፣ የመሥዋዕቱን አንድ ዐምስተኛ ጨምሮ ለካህኑ ይተካ። 15እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡትን የተቀደሰ መሥዋዕት ካህናቱ አያርክሱት፤ 16ይህንኑ የተቀደሰ መሥዋዕት እንዲበሉና ቅጣት የሚያስከትል በደል እንዲፈጽሙ አያድርጉ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”
ለእግዚአብሔር መቅረብ የማይገባው መሥዋዕት
17 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 18“ለአሮን፣ ለልጆቹና ለእስራኤላውያን በሙሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ከእናንተ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር መጻተኛ ስእለት ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማበርከት ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ቢሆን፣ 19መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው ከላም ወገን ወይም ከበጎች ወይም ከፍየሎች እንከን የሌለበትን ተባዕት ያቅርብ። 20እንከን ያለበትን ማንኛውንም ነገር አታቅርቡ፤ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት አይኖረውምና። 21ማንኛውም ሰው ስእለት ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማበርከት ከላም ወይም ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ ለእግዚአብሔር የኅብረት መሥዋዕት#22፥21 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል። ሲያቀርብ፣ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ፍጹም የሆነውንና እንከን የሌለበትን ያቅርብ። 22ዕውር ወይም ሰባራ ወይም ጕንድሽ ወይም ማንኛውንም ዐይነት እከክ ወይም ቋቍቻ ወይም የሚመግል ቍስል ያለበትን እንስሳ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ ከእነዚህ መካከል የትኛውንም በመሠዊያው ላይ በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ። 23አካሉ ከመጠን በላይ የረዘመን ወይም ያጠረን በሬ#22፥23 የዕብራይስጡ ቃል ተባዕትና እንስትን ሊያጠቃልል ይችላል። ወይም በግ የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጋችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ይሁን እንጂ ስእለት ለመፈጸም ተቀባይነት አይኖረውም። 24አባለዘሩ የተቀጠቀጠ ወይም የተኰላሸ፣ የተሰነጠቀ ወይም የተቈረጠ ማንኛውንም እንስሳ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ እነዚህንም በምድራችሁ አትሠዉ። 25እንደነዚህ ያሉትን እንስሳት ከባዕዳን በመቀበል ለአምላካችሁ ምግብ አድርጋችሁ አታቅርቡ፤ ነውር ስላለባቸው ፍጹም አይደሉምና ተቀባይነት አይኖራቸውም።’ ”
26 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 27“ጥጃ ወይም የበግ ግልገል ወይም የፍየል ግልገል በሚወለድበት ጊዜ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋራ ይቈይ፤ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ግን ተቀባይነት ያለው ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ይሆናል። 28ላምን ከጥጃዋ፣ በግንም ከግልገሏ ጋራ በአንድ ቀን አትረዱ።
29“ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጋችሁ አቅርቡት። 30መሥዋዕቱ በዚያ ዕለት ይበላ፤ ለሚቀጥለውም ቀን አታሳድሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
31“ትእዛዞቼን ጠብቁ፤ አድርጓቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 32ቅዱሱን ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ቅዱስ መሆኔ በእስራኤላውያን ዘንድ ይታወቅ፤ የምቀድሳችሁ#22፥32 ወይም የቀደስኋችሁ#22፥32 ወይም ቅዱስ አድርጌ የምለያችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 33አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.