ዘሌዋውያን 10

10
የናዳብና የአብዩድ መሞት
1የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ እያንዳንዳቸው ጥናዎቻቸውን ወስደው ፍም አደረጉባቸው፤ ዕጣንም ጨመሩባቸው፤ እርሱ ያላዘዛቸውን፣ ያልተፈቀደውን እሳት በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ። 2ከዚህም የተነሣ እሳት ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ በላቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ። 3ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር
“ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡት መካከል፣
ቅድስናዬን እገልጣለሁ፤
በሕዝቡም ሁሉ ፊት፣
እከበራለሁ’
ብሎ የተናገረው ይህን ነው።” አሮንም ዝም አለ።
4ሙሴ የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልዳፋንን ጠርቶ፣ “ወደዚህ ኑና ወንድሞቻችሁን አንሡ፤ ከመቅደሱም ደጃፍ አርቃችሁ፣ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዷቸው” አላቸው። 5እነርሱም መጥተው ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ ሟቾቹ የክህነት ቀሚሳቸውን እንደ ለበሱ ተሸክመው ከሰፈር ወደ ውጭ አወጧቸው።
6ሙሴም አሮንንና የአሮንን ልጆች፣ አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “እንዳትሞቱ፣ በሕዝቡም ላይ ቍጣ እንዳይመጣ ጠጕራችሁን አትንጩ፤#10፥6 ወይም አትላጩ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በእሳት ስላጠፋቸው ሰዎች ወንድሞቻችሁ እስራኤላውያን ሊያለቅሱላቸው ይችላሉ። 7እግዚአብሔር የመቅቢያ ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን አትውጡ።” እነርሱም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ።
8 እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ አለው፤ 9“እንዳትሞቱ አንተና ልጆችህ ወደ መገናኛው ድንኳን በምትገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ፤ ይህም በልጅ ልጃችሁ ዘንድ የሚጠበቅ ዘላለማዊ ሥርዐት ነው። 10የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን፣ ርኩሱንና ንጹሑን ለዩ፤ 11እግዚአብሔርም በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውን ሥርዐት ሁሉ ለእስራኤላውያን አስተምሩ።”
12ሙሴም አሮንንና የተረፉትን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “በእሳት ለእግዚአብሔር ከቀረበው የእህል ቍርባን የቀረውን ወስዳችሁ ቂጣ ጋግሩ፤ እጅግ ቅዱስ ስለ ሆነ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት። 13እግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት ያንተና የልጆችህ ድርሻ ይህ ስለ ሆነ፣ በተቀደሰ ስፍራ ብሉት፤ እንዲህ ታዝዣለሁና። 14ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት#10፥14 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል ላይ የእናንተ ድርሻ ሆኖ ስለ ተሰጠ፣ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ብሉት። 15የቀረበውን ወርችና የተወዘወዘውን ፍርምባ በእግዚአብሔር ፊት የመወዝወዝ መሥዋዕት ሆኖ በእሳት ከቀረበው ሥብ ጋራ ይምጣ። ይህም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም የተመደበ ድርሻ ይሆናል።”
16ሙሴ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚቀርበውን ፍየል አጥብቆ ፈለገ፤ መቃጠሉንም በተረዳ ጊዜ የተረፉትን የአሮንን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን ተቈጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ 17“የኀጢአት መሥዋዕቱን ለምን በተቀደሰው ስፍራ አልበላችሁትም? እጅግ የተቀደሰ ነው፤ በእግዚአብሔር ፊት ስርየት በማስገኘት የሕዝቡን ኀጢአት እንድታስወግዱበት የተሰጣችሁ ነበር፤ 18ደሙ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ስላልገባ፣ በሰጠሁት ትእዛዝ መሠረት ፍየሉን በተቀደሰው ስፍራ መብላት ይገባችሁ ነበር።”
19አሮንም ሙሴን፣ “እነሆ፤ በዛሬው ቀን የኀጢአት መሥዋዕታቸውንና የሚቃጠል መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፤ እኔም እንዲህ ያለ ነገር የደረሰብኝ ሰው ነኝ፤ ታዲያ፣ ዛሬ የኀጢአት መሥዋዕቱን ብበላ ኖሮ እግዚአብሔርስ ደስ ይለው ኖሯልን?” አለው። 20ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ መልሱ አረካው።

Currently Selected:

ዘሌዋውያን 10: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ