ኢዮብ 12
12
ኢዮብ
1ኢዮብ እንዲህ ሲል መለሰ፤
2“በርግጥ ሰው ማለት እናንተ ናችኋ!
ጥበብም ከእናንተ ጋራ ትሞታለቻ!
3ነገር ግን እኔም እንደ እናንተ አእምሮ አለኝ፤
ከእናንተ አላንስም፤
እንዲህ ያለውን ነገር የማያውቅ ማን ነው?
4“እግዚአብሔርን ጠርቼ የመለሰልኝ ሰው ብሆንም፣
ለባልንጀሮቼ መሣቂያ ሆኛለሁ፤
ጻድቅና ያለ ነቀፋ ሆኜ እያለሁ፣ መሣቂያ ሆኛለሁ።
5የደላቸው በመከራ ያፌዛሉ፤
እግሩ የተንሸራተተውንም ይገፈትራሉ።
6የቀማኞች ድንኳን አይታወክም፤
አምላካቸውን በእጃቸው ይዘው እየዞሩም፣#12፥6 ወይም የእግዚአብሔር እጅ በምታመጣላቸው ነገር
እግዚአብሔርንም እያስቈጡ በሰላም ይኖራሉ።
7“እስኪ እንስሳትን ጠይቁ፤ ያስተምሯችኋል፤
የሰማይ ወፎችንም ጠይቁ፣ ይነግሯችኋል፤
8ለምድር ተናገሩ፤ ታስተምራችኋለች፤
የባሕርም ዓሣ ይነግራችኋል።
9የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ፣
ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?
10የፍጥረት ሁሉ ሕይወት፣
የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናትና፤
11ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፣
ጆሮ ቃላትን አይለይምን?
12ጥበብ ያለው በአረጋውያን ዘንድ አይደለምን?
ማስተዋልስ ረዥም ዕድሜ ባላቸው ዘንድ አይገኝምን?
13“ጥበብና ኀይል የእግዚአብሔር ናቸው፤
ምክርና ማስተዋልም በርሱ ዘንድ ይገኛሉ።
14እርሱ ያፈረሰውን መልሶ የሚገነባ የለም፣
እርሱ ያሰረውን የሚፈታ አይገኝም።
15እርሱ ውሃን ቢከለክል፣ ድርቅ ይሆናል፤
ቢለቅቀውም ውሃው ምድሪቱን ያጥለቀልቃል።
16ብርታትና ጥበብ ማድረግ በርሱ ዘንድ ይገኛል፤
አታላዩም ተታላዩም በርሱ እጅ ናቸው።
17አማካሪዎችን ከጥበባቸው ያራቍታል፤
ፈራጆችንም ማስተዋል ይነሣል።
18ነገሥታትን ድግ ያስፈታል፤
ገመድም በወገባቸው ያስራል።#12፥18 ወይም የነገሥታትን ድግ፤ ሠቅ ያስራል
19ካህናትን ከክህነታቸው ያዋርዳል፤
ለዘመናት የተደላደሉትንም ይገለብጣል።
20የታመኑ መካሪዎችን ቋንቋ ያሳጣል፤
የሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይወስዳል።
21የተከበሩትን ውርደት ያከናንባል፤
ብርቱዎችንም ትጥቅ ያስፈታል።
22የጨለማን ጥልቅ ነገሮች ይገልጣል፤
የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ያወጣል።
23ሕዝቦችን ታላቅ ያደርጋል፤ መልሶም ያጠፋቸዋል፤
ሕዝቦችን ያበዛል፤ ያፈልሳቸዋልም።
24የዓለም መሪዎችን ማስተዋል ይነሣል፣
መንገድ በሌለበት በረሓም ያቅበዘብዛቸዋል፤
25ብርሃን በሌለበት ጨለማ በዳበሳ ይሄዳሉ፤
እንደ ሰካራምም ይንገዳገዳሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.