ኤርምያስ 41

41
1ከንጉሣዊ ቤተ ሰብ የሆነው ከንጉሡ የጦር መኰንንኖች አንዱ የነበረው የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ በሰባተኛው ወር ከዐሥር ሰዎች ጋራ ወደ ምጽጳ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ፤ በዚያም በአንድነት ሊበሉ በማእድ ተቀምጠው ሳለ፣ 2የናታንያ ልጅ እስማኤልና ዐብረውት የነበሩ ዐሥሩ ሰዎች ተነሥተው፣ የባቢሎን ንጉሥ በምድሪቱ ላይ ገዥ አድርጎ የሾመውን የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መቱት፤ ገደሉትም። 3ደግሞም እስማኤል በምጽጳ ከጎዶልያስ ጋራ የነበሩትን አይሁድ ሁሉ፣ በዚያም የተገኙትን የባቢሎን#41፥3 ወይም የከለዳውያን ወታደሮች ገደላቸው።
4ጎዶልያስ በተገደለ ማግስት፣ ማንም ስለ ሁኔታው ከማወቁ በፊት፣ 5ሰማንያ ሰዎች ጢማቸውን ተላጭተው፣ ልብሳቸውን ቀድደው፣ ገላቸውን ነጭተው የእህል ቍርባንና ዕጣን በመያዝ ከሴኬም፣ ከሴሎና ከሰማርያ ወደ እግዚአብሔር ቤት ለማቅረብ መጡ። 6የናታንያ ልጅ እስማኤል ሊገናኛቸው እያለቀሰ ከምጽጳ ወጣ፤ ሲያገኛቸውም፣ “ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑ” አላቸው። 7ወደ ከተማዪቱ በገቡ ጊዜ፣ የናታንያ ልጅ እስማኤልና ዐብረውት የነበሩ ሰዎች ዐረዷቸው፤ በውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ ውስጥም ጣሏቸው። 8ከተገደሉት ጋራ የነበሩ ዐሥር ሰዎች ግን እስማኤልን፣ “እባክህ አትግደለን! በዕርሻችን ውስጥ የሸሸግነው ስንዴና ገብስ፣ የወይራ ዘይትና ማር ስላለን እባክህን አትግደለን” አሉት። እርሱም ተዋቸው፤ ከሌሎቹም ጋራ አልገደላቸውም። 9እስማኤል ከጎዶልያስ በተጨማሪ የገደላቸው ሰዎች ሁሉ ሬሳ የተጣለበት የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ፣ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ስለ ፈራ ለመከላከል ያሠራው ነበር፤ ይህን ጕድጓድ የናታንያ ልጅ እስማኤል በሬሳ ሞላው።
10እስማኤል በምጽጳ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ምርኮኛ አደረገ፤ እነርሱም የባቢሎን የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው ገዥ አድርጎ የሾመባቸው የንጉሡ ሴቶች ልጆችና በዚያ የቀሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ ነበሩ። የናታንያ ልጅ እስማኤል እነዚህን ማርኮ ወደ አሞናውያን ለመሻገር ተነሣ።
11የቃሬያ ልጅ ዮሐናና ከርሱ ጋራ የነበሩት የጦር መኰንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የፈጸመውን ግፍ ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ 12የናታንያን ልጅ እስማኤልን ሊወጉ ሰዎቻቸውን ሁሉ ይዘው ሄዱ፤ በገባዖንም ባለው በታላቁ ኵሬ አጠገብ ደረሱበት። 13እስማኤል የያዛቸው ሰዎች ሁሉ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንንና ዐብረውት የነበሩትን የጦር መኰንኖች ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 14እስማኤል ከምጽጳ ማርኮ የወሰዳቸው ሰዎች ሁሉ አምልጠው ወደ ቃሬያ ልጅ ወደ ዮሐናን ገቡ። 15የናታንያ ልጅ እስማኤል ግን ዐብረውት ከነበሩት ስምንት ሰዎች ጋራ ከዮሐናን አመለጠ፤ ሸሽቶም ወደ አሞናውያን ገባ።
ሽሽት ወደ ግብጽ
16የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና ከርሱ ጋራ የነበሩት የጦር መኰንኖች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ፣ በምጽጳ ከማረካቸው የተረፉትን ሰዎች በማስመለስ ይዘው ሄዱ፤ እነዚህም፣ ወታደሮች፣ ሴቶች ሕፃናትና ከገባዖን ያመጧቸው የቤተ መንግሥት ባለሥልጣኖች ነበሩ። 17ከዚያም ተነሥተው ሄዱ፤ ወደ ግብጽም በማምራት በቤተ ልሔም አጠገብ ባለችው በጌሮት ከመዓም ዐረፉ፤ 18ወደ ግብጽም የሄዱት ከባቢሎናውያን#41፥18 ወይም ከከለዳውያን ለማምለጥ ነበር፤ ባቢሎናውያንንም የፈሩት የናታንያ ልጅ እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ የምድሪቱ ገዥ አድርጎ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በመግደሉ ነው።

Currently Selected:

ኤርምያስ 41: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ