ሆሴዕ 2

2
1“ወንድሞቻችሁን ‘ሕዝቤ’፣ እኅቶቻችሁንም ‘ተወዳጆቼ’ ብላችሁ ጥሯቸው።
የእስራኤል መቀጣትና መመለስ
2“እናታችሁን ምከሯት፤ ምከሯት፤
እርሷ ሚስቴ አይደለችም፤
እኔም ባሏ አይደለሁምና።
ከፊቷ የዘማዊነት አስተያየትን፣
ከጡቶቿም መካከል ምንዝርናዋን ታስወግድ።
3አለዚያ ገፍፌ ዕርቃኗን አስቀራታለሁ፤
እንደ ተወለደችበትም ቀን አደርጋታለሁ፤
እንደ ምድረ በዳ፣
እንደ ደረቅም ምድር አደርጋታለሁ፤
በውሃ ጥምም እገድላታለሁ።
4ለልጆቿ አልራራላቸውም፤
የምንዝርና ልጆች ናቸውና።
5እናታቸው አመንዝራ ናት፤
በውርደትም ፀንሳቸዋለች፤
እርሷም፣ ‘እንጀራዬንና ውሃዬን ይሰጡኛል፤
ሱፌንና የሐር ልብሴን፣ ዘይቴንና መጠጤን ይሰጡኛል፤
ስለዚህ ውሽሞቼን ተከትዬ እሄዳለሁ’ አለች።
6በዚህ ምክንያት መንገዷን በእሾኽ እዘጋለሁ፤
መውጫ መንገድ እንዳታገኝም ዙሪያዋን በግንብ ዐጥራለሁ።
7ውሽሞቿን ተከትላ ትሄዳለች፤ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤
ትፈልጋቸዋለች፤ ሆኖም አታገኛቸውም።
ከዚያም እንዲህ ትላለች፤
‘ወደ ቀድሞ ባሌ እመለሳለሁ፤
የፊተኛው ኑሮዬ ከአሁኑ ይሻለኛልና።’
8እርሷም እህል፣ ዘይትና አዲስ የወይን ጠጅ የሰጠኋት፣
ለበኣል አምልኮ ያደረጉትን፣
ብርንና ወርቅን ያበዛሁላት፣
እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም።
9“ስለዚህ እህሌን በመከር ጊዜ፣
አዲሱም የወይን ጠጅ በደረሰ ጊዜ እወስዳለሁ፤
ዕርቃኗንም እንዳትሸፍንበት፣
ሱፍና የሐር ልብሴን መልሼ እወስድባታለሁ።
10አሁንም በውሽሞቿ ፊት፣
ነውሯን እገልጣለሁ፤
ከእጄም የሚያድናት የለም።
11የደስታ በዓሎቿን ሁሉ፣
የዓመት በዓላቷንና የወር መባቻዎቿን፣
ሰንበቶቿንና የተመረጡ በዓላቷን ሁሉ አስቀራለሁ።
12ከውሽሞቼ የተቀበልሁት ዋጋ ነው የምትለውን
የወይን ተክሎቿንና የበለስ ዛፎቿን አጠፋለሁ፤
ጫካ አደርገዋለሁ፤
የዱር አራዊትም ይበሉታል።
13ለበኣል አማልክት ዕጣን ስላጠነችባቸው ቀናት
እቀጣታለሁ፤
በጌጣጌጥና በቀለበቶች ራሷን አስጊጣለች፤
ውሽሞቿንም ተከትላ ሄዳለች፤
እኔን ግን ረስታለች” ይላል እግዚአብሔር
14“ስለዚህ እነሆ፤ አባብላታለሁ፤
ወደ ምድረ በዳም እወስዳታለሁ፤
በፍቅር ቃል አነጋግራታለሁ።
15በዚያም የወይን ተክሏን እመልስላታለሁ፤
የአኮርንም#2፥15 አኮር ማለት ችግር ማለት ነው ሸለቆ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ።
በዚያም ከግብጽ እንደ ወጣችበት ቀን፣
እንደ ልጅነቷም ጊዜ ትዘምራለች።#2፥15 ወይም ትሆናለች
16“በዚያ ቀን፣ ‘ባሌ’ ብለሽ፣
ትጠሪኛለሽ” ይላል እግዚአብሔር
“ከእንግዲህም፣ ‘ጌታዬ’#2፥16 ዕብራይስጡ በኣል ይላል ብለሽ አትጠሪኝም።
17የበኣል አማልክትን ስም ከአንደበቷ አስወግዳለሁ፤
ከእንግዲህም ስሞቻቸው አይነሡም።
18በዚያ ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፣
በምድርም ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ጋራ፣
ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤
ሁሉም ያለ ሥጋት እንዲኖሩ፣
ቀስትን፣ ሰይፍንና ጦርነትን፣
ከምድሪቱ አስወግዳለሁ።
19ለእኔ እንድትሆኚ ለዘላለም ዐጭሻለሁ፤
በጽድቅና በፍትሕ፣
በፍቅርና በርኅራኄም ዐጭሻለሁ።
20በታማኝነት ዐጭሻለሁ፤
አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂያለሽ።”
21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“በዚያ ቀን እኔ እመልሳለሁ፤
ለሰማያት እመልሳለሁ፤
እነርሱም ለምድር ምላሽ ይሰጣሉ፤
22ምድርም ለእህል፣
ለአዲስ የወይን ጠጅና ለዘይት ምላሽ ትሰጣለች፤
እነርሱም ለኢይዝራኤል#2፥22 ኢይዝራኤል ማለት እግዚአብሔር ይተክላል ማለት ነው ምላሽ ይሰጣሉ።
23ስለ ራሴ ስል በምድሪቱ እተክላታለሁ፤
‘ምሕረትን ያላገኘ’#2፥23 ዕብራይስጡ ሎሩሃማ ይላል ብዬ የጠራሁትንም እምረዋለሁ፤
‘ሕዝቤ አይደላችሁም’#2፥23 ዕብራይስጡ ሎዓሚ ይላል ተብለው የተጠሩትንም፣ ‘ሕዝቤ’ እላቸዋለሁ፤
እነርሱም፣ ‘አንተ አምላኬ ነህ’ ይላሉ።”

Currently Selected:

ሆሴዕ 2: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ