ገላትያ 2:14-21

ገላትያ 2:14-21 NASV

ተግባራቸው እንደ ወንጌል እውነት አለመሆኑን በተረዳሁ ጊዜ፣ በሁሉም ፊት ኬፋን እንዲህ አልሁት፤ “አንተ አይሁዳዊ ነህ፤ ሆኖም በአሕዛብ ሥርዐት እንጂ በአይሁድ ሥርዐት አትኖርም፤ ታዲያ አሕዛብ የአይሁድን ሥርዐት እንዲከተሉ እንዴት ታስገድዳቸዋለህ? “እኛ በትውልዳችን አይሁድ እንጂ፣ ‘ኀጢአተኞች አሕዛብ’ ያልሆንን፣ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ፣ ሕግን በመጠበቅ እንደማይጸድቅ እናውቃለን። ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን እንጸድቅ ዘንድ እኛም ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፤ ሕግን በመጠበቅ ማንም አይጸድቅምና። “በክርስቶስ ለመጽደቅ ስንፈልግ፣ እኛ ራሳችን ኀጢአተኞች መሆናችን ግልጽ ነው፤ ታዲያ ክርስቶስ ኀጢአት እንዲስፋፋ ያደርጋልን? ከቶ አይሆንም! ያፈረስሁትን መልሼ የምገነባ ከሆነማ፣ ሕግ ተላላፊ መሆኔን አረጋግጣለሁ። “ለእግዚአብሔር እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቻለሁና። ከክርስቶስ ጋራ ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ አላቃልልም፤ ጽድቅ በሕግ በኩል የሚገኝ ከሆነማ፣ ክርስቶስ እንዲያው በከንቱ ሞተ ማለት ነዋ!”