ዘፀአት 4

4
ለሙሴ የተሰጡ ምልክቶች
1ሙሴም “ባያምኑኝስ፤ ቃሌን ባይቀበሉስ፤ ‘እግዚአብሔር አልተገለጠልህም’ ቢሉኝስ?” ብሎ መለሰ።
2 እግዚአብሔርም፣ “በእጅህ የያዝሃት እርሷ ምንድን ናት?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም መልሶ፣ “በትር ናት” አለው።
3 እግዚአብሔርም፣ “መሬት ላይ ጣላት” አለው።
ሙሴ በትሩን መሬት ላይ ጣላት፤ እባብም ሆነች፤ ከአጠገቧም ሸሸ። 4እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በል እጅህን ዘርጋና ጅራቷን ያዛት” አለው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ሲይዛት እባቧ ተለውጣ በእጁ ላይ እንደ ገና በትር ሆነች። 5እግዚአብሔርም “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር የተገለጠልህ መሆኑን እንዲያምኑ ነው” አለው።
6 እግዚአብሔርም ደግሞ፣ “እጅህን ብብትህ ውስጥ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ#4፥6 በዕብራይስጥ፣ ለምጽ የሚባለው ቈዳን ለሚያጠቁ በሽታዎች ሁሉ የሚውል እንጂ ቍምጥናን ወይም ለምጽን የሚያሳይ አይደለም። ሆነች።
7“አሁንም ደግሞ እጅህን ወደ ብብትህ መልሰህ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን መልሶ ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ እንደ ገና እጁን ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ፣ ተመልሳ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነች።
8 እግዚአብሔርም፣ “እንግዲህ ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ታምራዊ ምልክት ባይቀበሉ እንኳ ሁለተኛውን ያምናሉ። 9እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ወይም ቃልህን ባይቀበሉ ግን፣ ከአባይ ወንዝ ጥቂት ውሃ ቀድተህ በደረቅ ምድር ላይ አፍስሰው። ከወንዙም ቀድተህ ያፈሰስኸው ውሃ በምድር ላይ ደም ይሆናል።”
10ሙሴም እግዚአብሔርን፣ “ጌታ ሆይ፤ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋራ ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኰልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” አለው።
11 እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቈሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዐይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? 12በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው።
13ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው።
14በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ፤ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደል? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልቡ ደስ ይለዋል። 15ለርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገራቸውንም ቃላት በአንደበቱ ታኖራለህ፤ ሁለታችሁም በትክክል እንድትናገሩ ረዳችኋለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ። 16አንተ እንደ አምላኩ ሆነህ ትነግረዋለህ፤ እርሱም እንደ አንደበትህ ሆኖ ለሕዝቡ ይናገርልሃል። 17ታምራዊ ምልክት እንድታሳይባት ይህችን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ።”
ሙሴ ወደ ግብጽ ተመለሰ
18ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ ሄደና፣ “ወገኖቼ እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን አይ ዘንድ ወደ ግብጽ ተመልሼ እንድሄድ እባክህ ፍቀድልኝ” አለው።
ዮቶርም፣ “ሂድ፤ በሰላም ያግባህ” አለው።
19ሙሴ በምድያም ሳለ እግዚአብሔር፣ “አንተን ሊገድሉህ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብጽ ሂድ” አለው። 20ስለዚህ ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ፣ ወደ ግብጽ አገር መመለስ ጀመረ፤ የእግዚአብሔርም በትር በእጁ ይዞ ነበር።
21 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፣ “ወደ ግብጽ በምትመለስበት ጊዜ በሰጠሁህ ኀይል የምትሠራቸውን ታምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ። እኔ ግን ሕዝቡን እንዳይለቅ ልቡን አደነድነዋለሁ። 22ስለዚህ ለፈርዖን እንዲህ በለው፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ 23ያመልከኝ ዘንድ ልጄን ልቀቀው” ብዬህ ነበር፤ አንተ ግን እንዳይሄድ ከለከልኸው፤ ስለዚህ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ።’ ”
24ሙሴ#4፥24 ወይም፣ የሙሴ ልጅ ሊሆን ይችላል። ዕብራይስጡ፣ እርሱ ይላል። በጕዞ ላይ በእንግዳ ማረፊያ ስፍራ ውስጥ ሳለ እግዚአብሔር አግኝቶት ሊገድለው ፈልጎ ነበር። 25ሚስቱ ሲፓራ ግን ስለታም ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ በሸለፈቱ የሙሴን እግር በመንካትም#4፥25 ወይም ወደ ሙሴ እግር በመቅረብም ሊባል ይችላል። “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራዬ ነህ” አለችው። 26ስለዚህም እግዚአብሔር ተወው፤ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” ያለችው በግርዛቱ ምክንያት ነው።
27 እግዚአብሔር አሮንን፣ “ሙሴን እንድታገኘው ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው። እርሱም ሙሴን በእግዚአብሔር ተራራ አገኘው፤ ሳመውም። 28ሙሴም እግዚአብሔር እንዲናገር የላከውን ቃል በሙሉና እንዲፈጽማቸው ስላዘዘው ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው።
29ሙሴና አሮን ሄዱና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ፤ 30አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል በሙሉ ነገራቸው፤ ታምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። 31ሕዝቡም አመኑ፣ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች እንደ ጐበኛቸውና መከራቸውን እንዳየ በሰሙ ጊዜ ተንበረከኩ፤ በስግደትም አመለኩት።

Currently Selected:

ዘፀአት 4: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ