ዘፀአት 36
36
1ስለዚህ የመቅደሱን የግንባታ ሥራ ሁሉ እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው እግዚአብሔር ጥበብንና ችሎታን የሰጣቸው፣ ባስልኤል፣ ኤልያብና ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ሥራውን ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ይሥሩት።”
2ከዚያም ሙሴ ባስልኤልንና ኤልያብን እንዲሁም እግዚአብሔር ችሎታ የሰጣቸውን፣ መጥተው ሥራውን ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑትን ጥበብ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ አስጠራ። 3የመቅደሱን የግንባታ ሥራ ለማከናወን እስራኤላውያን ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ከሙሴ ተቀበሉ፤ ሕዝቡ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን በየማለዳው ማምጣታቸውን ቀጠሉ። 4ስለዚህ የመቅደሱን ሥራ ሁሉ ይሠሩ የነበሩ ጥበበኞች የሆኑ ባለሙያዎች ሁሉ ሥራቸውን ትተው መጡ፤ 5ሙሴንም፣ “ሕዝቡ እግዚአብሔር እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ እያመጡ ነው” አሉት።
6ከዚያም ሙሴ ትእዛዝ ሰጠ፤ ይህንም ቃል ወደ ሰፈሩ ላኩት፤ “ማንም ወንድ ወይም ሴት ለመቅደሱ ሌላ ምንም ስጦታ ማድረግ የለበትም፤” ስለዚህ ሕዝቡ ትርፍ እንዳያመጡ ተከለከሉ፤ 7ምክንያቱም ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በእጃቸው ያለው ከበቂ በላይ ነበረ።
የማደሪያው ድንኳን
36፥8-38 ተጓ ምብ – ዘፀ 26፥1-37
8የሥራ ችሎታ ካላቸው ሰዎች መካከል ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የማደሪያውን ድንኳን በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በጥልፍ ዐዋቂ፣ ኪሩቤል ከተጠለፉበት ከዐሥር መጋረጃዎች ሠሩት። 9መጋረጃዎቹም ሁሉ ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ሲሆን፣ ቁመታቸው ሃያ ስምንት ክንድ፣ ወርዳቸው አራት ክንድ#36፥9 ቁመቱ 13 ሜትር፣ ወርዱ 1.8 ሜትር ይህል ማለት ነው። ነበር። 10ዐምስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ በማጋጠም ሰፏቸው፤ የቀሩትን ዐምስቱንም እንዲሁ አደረጉ። 11ተጋጥሞ ከተሰፋው መጋረጃ ጠርዝ ጫፍ ላይ ከሰማያዊ ግምጃ ቀለበቶችን አበጁ፤ ተጋጥሞ በተሰፋው በሌላው መጋረጃ ጫፍ ላይም ተመሳሳይ ነገር አደረጉ። 12በአንደኛው መጋረጃ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን በሌላው ተጋጥሞ ከተሰፋው በስተመጨረሻ ካለው መጋረጃ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን እርስ በርሳቸው ትይዩ በማድረግ ሠሩት። 13ከዚያም ዐምሳ የወርቅ ማያያዣዎችን ሠሩ፤ የማደሪያው ድንኳን አንድ ወጥ ይሆን ዘንድም ተጋጥመው የተሰፉትን ሁለቱን መጋረጃዎች አያያዙባቸው።
14ከማደሪያው በላይ ለሚሆነው ድንኳን ከፍየል ቈዳ የተሠሩ በጠቅላላ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችን ሠሩ። 15ዐሥራ አንዱ መጋረጃዎች ተመሳሳይ ልክ ሲኖራቸው፣ ቁመታቸው ሠላሳ ክንድ፣ ወርዳቸውም አራት ክንድ#36፥15 ቁመቱ 14 ሜትር፣ ወርዱ 1.8 ሜትር ያህል ማለት ነው። ነበር። 16ዐምስቱን መጋረጃዎች በአንድ በኩል፣ ሌሎቹን ስድስት መጋረጃዎች ደግሞ በሌላ በኩል አንድ ላይ አያያዟቸው። 17በስተመጨረሻ በሚገኘው መጋረጃ ጠርዝ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን፣ በሌላ በኩል ባለው በስተመጨረሻ በሚገኘው መጋረጃ ጠርዝ ዐምሳ ቀለበቶችን አበጁ። 18ድንኳኑን አንድ ወጥ አድርጎ ለማያያዝም ዐምሳ የንሓስ ማያያዣዎችን ሠሩ። 19ከዚያም ለድንኳኑ መሸፈኛ የሚሆን ቀይ ከተነከረ የአውራ በግ ቈዳ ሠሩ፤ በላዩ ላይ የሚሆንም የአቆስጣ ቈዳ#36፥19 ይህ የባሕር አውሬ ነው፤ አበጁ።
20ለማደሪያው ድንኳን ከግራር ዕንጨት ወጋግራዎችን አበጁ። 21እያንዳንዱም ወጋግራ ቁመቱ ዐሥር ክንድ፣ ስፋቱ አንድ ክንድ ተኩል#36፥21 ቁመቱ 4.5 ሜትር ወርዱ 68 ሳንቲ ሜትር ያህል ማለት ነው። ነበር፤ 22ትይዩ የሆኑ ሁለት ጕጦች ነበሩት፤ የማደሪያውን ድንኳን ወጋግራዎች በዚህ መልክ ሠሩ። 23በደቡብ በኩል ላለው የማደሪያው ድንኳን ሃያ ወጋግራዎችን አበጁ፤ 24ለእያንዳንዱ ጕጠት አንድ መቆሚያ፣ ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያ ሆኖ አርባ የብር መቆሚያዎችን አበጁ። 25በስተሰሜን በኩል ላለው የማደሪያው ድንኳን ሃያ ወጋግራዎችን ሠሩ፤ 26ለእያንዳንዱ ወጋግራ ሁለት መቆሚያ የሆኑ አርባ የብር መቆሚያዎችን ሠሩ። 27በዳር በኩል ይኸውም በስተምዕራብ ጫፍ ባለው ማደሪያው ድንኳን ስድስት ወጋግራዎችን ሠሩ። 28ዳርና ዳር ላሉት የማደሪያው ድንኳን ማእዘኖችም ሁለት ወጋግራዎችን ሠሩ። 29በእነዚህ ሁለት ማእዘኖች ላይ ከታች አንሥቶ እስከ ላይ ድረስ ወጋግራዎቹ በአንድ ላይ ተነባብረው በአንድ ቀለበት ውስጥ ተገጥመው ነበር፤ ሁለቱም አንድ አካል ሆነው ተሠርተው ነበር። 30ስለዚህ ስምንት ወጋግራዎችና ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያዎች ሆነው ዐሥራ ስድስት የብር መቆሚያዎች ነበሩ።
31እንደዚሁም ከግራር ዕንጨት አግዳሚዎችን ሠሩ፤ በማደሪያው ድንኳን በአንድ በኩል ላሉት ወጋግራዎች ዐምስት አግዳሚዎችን ሠሩ፤ 32በሌላ በኩል ላሉት ዐምስት አግዳሚዎች፣ በምዕራብ በኩል በማደሪያው ድንኳን ዳር ላይ ላሉት ወጋግራዎች ዐምስት አግዳሚዎችን ሠሩ። 33በወጋግራዎቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር እንዲዘረጋ ሆኖ መካከለኛውን አግዳሚ ሠሩ። 34ወጋግራዎቹን በወርቅ ለበጧቸው፤ አግዳሚዎቹን ለመያዝም የወርቅ ቀለበቶችን ሠሩ፤ እንዲሁም አግዳሚዎቹን በወርቅ ለበጧቸው።
35ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ፣ እጀ ጥበብ ባለሙያም ኪሩቤል የተጠለፉበት መጋረጃ ሠራ። 36ለርሱም አራት ምሰሶዎች ከግራር ዕንጨት ሠርተው በወርቅ ለበጧቸው፤ ለእነርሱም አራት የወርቅ ኵላቦችንና አራት የብር መቆሚያዎችን አበጁላቸው። 37በድንኳኑ መግቢያ ጥልፍ ጠላፊ እንደሚሠራው ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አበጁለት፤ 38ለእነርሱም ኵላቦች ያሏቸው ዐምስት ምሰሶዎች ሠሩላቸው፤ የምሰሶዎቹን ዐናቶችና ዘንጎች በወርቅ በመለበጥ ዐምስቱን መቆሚያዎች ከንሓስ ሠሩ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.