አስቴር 6
6
መርዶክዮስ ከፍ ከፍ አለ
1በዚያች ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ መተኛት አልቻለም። ስለዚህ በዘመነ መንግሥቱ የተመዘገበው የታሪክ መጽሐፍ ቀርቦ እንዲነበብለት አዘዘ። 2በዚያም በሩን ከሚጠብቁት ከንጉሡ የጦር አዛዦች ሁለቱ፣ ገበታና ታራ ንጉሥ ጠረክሲስን ለመግደል አሢረው እንደ ነበርና ይህንም መርዶክዮስ እንደ ተናገረ ተጽፎ ተገኘ።
3ንጉሡም፣ “ታዲያ ይህን በማድረጉ መርዶክዮስ ያገኘው ክብርና ማዕርግ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።
የቅርብ አገልጋዮቹም፣ “ምንም አልተደረገለትም” ብለው መለሱ።
4ንጉሡም፣ “በአደባባዩ ማን አለ?” ሲል ጠየቀ። በዚህ ጊዜ ሐማ በተከለው ዕንጨት ላይ መርዶክዮስ ይሰቀል ዘንድ ለንጉሡ ለመናገር በውጭ በኩል ወደሚገኘው የቤተ መንግሥቱ አደባባይ ገና መድረሱ ነበር።
5የቅርብ አገልጋዮቹም፣ “እነሆ፤ ሐማ በአደባባዩ ቆሟል” አሉት።
ንጉሡም፣ “ግባ በሉት” ብሎ አዘዘ።
6ሐማ በገባ ጊዜ ንጉሡ፣ “ንጉሥ ሊያከብረው ለወደደው ሰው ምን ሊደረግለት ይገባል?” ሲል ጠየቀው።
በዚህ ጊዜ ሐማ፣ “ንጉሡ ከእኔ ይልቅ የሚያከብረው ማን አለ?” ሲል በልቡ ዐሰበ። 7ስለዚህ ሐማ ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንጉሡ ሊያከብረው ለወደደው ሰው፣ 8ንጉሡ የሚጐናጸፈው ልብሰ መንግሥት፣ ንጉሡም የሚቀመጥበትና የንጉሡን ዘውድ በራሱ ላይ ያደረገ ፈረስ ይምጣለት። 9ከዚያም ልብሱና ፈረሱ እጅግ ከከበሩት ከንጉሡ ልዑላን መሳፍንት በአንዱ እጅ ይሰጥለት። ንጉሡ ሊያከብረው የወደደውን ሰው ያልብሱት፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጠውም በከተማዪቱ ዋና ዋና መንገዶች ላይ እየመሩ፣ ‘ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው ይህ ተደርጎለታል’ ይበሉ።”
10ንጉሡም ሐማን፣ “በል ፈጥነህ ሂድ፤ ልብሱንና ፈረሱን ውሰድ፤ በንጉሡ በር ላይ ለሚቀመጠው ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስም ልክ እንዳልኸው አድርግለት፤ ከተናገርኸውም አንዳች ነገር እንዳይጐድል” ሲል አዘዘው።
11ስለዚህ ሐማ ልብሱንና ፈረሱን ወስዶ መርዶክዮስን አለበሰው፤ በዋና ዋና መንገዶች ላይ እየመራም፣ “ንጉሥ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው ይህ ተደርጎለታል” እያለ በፊቱ ያውጅ ነበር።
12ከዚያም በኋላ መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ በር ተመለሰ፤ ሐማ ግን ዐዝኖና ራሱን ተከናንቦ በጥድፊያ ወደ ቤቱ ሄደ። 13ሐማም የደረሰበትን ሁሉ ለሚስቱ ለዞሳራና ለወዳጆቹ ሁሉ ነገራቸው።
አማካሪዎቹና ሚስቱ ዞሳራም፣ “በፊቱ መውደቅ የጀመርህለት መርዶክዮስ ዘሩ ከአይሁድ ወገን ከሆነ፣ ልትቋቋመው አትችልም፤ ያለ ጥርጥር ትጠፋለህ” አሉት። 14ከርሱ ጋራ በመነጋገር ላይ ሳሉ፣ የንጉሡ ጃንደረቦች ደርሰው ሐማን አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ አጣደፉት።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.