አስቴር 5
5
አስቴር ለንጉሡ ያቀረበችው ልመና
1በሦስተኛው ቀን አስቴር የክብር ልብሷን ለብሳ በንጉሡ አዳራሽ ፊት ለፊት ባለው በቤተ መንግሥቱ ውስጠኛ አደባባይ ገብታ ቆመች። ንጉሡም አዳራሹ ውስጥ በመግቢያው ትይዩ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር። 2ንግሥት አስቴር በአደባባዩ ላይ ቆማ ሲያያት ደስ አለው፤ በእጁ የያዘውን የወርቅ ዘንግ ዘረጋላት፤ አስቴርም ቀረብ ብላ የዘንጉን ጫፍ ነካች።
3ከዚያም ንጉሡ፣ “ንግሥት አስቴር ሆይ፤ ለምን መጣሽ? ከእኔ የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይሰጥሻል” አላት።
4አስቴርም መልሳ፣ “ንጉሡን ደስ የሚያሠኘው ቢሆን፣ ባዘጋጀሁለት ግብዣ ላይ ንጉሡ ዛሬ ከሐማ ጋራ ይገኝልኝ” አለች።
5ንጉሡም፣ “አስቴር ያለችውን እንድንፈጽም፣ ሐማን በፍጥነት ጥሩት” አለ። ስለዚህ ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ሄዱ። 6የወይን ጠጅ እየጠጡ ሳለ ንጉሡ ዳግመኛ አስቴርን፣ “እስኪ የምትፈልጊው ምንድን ነው? ይሰጥሻል፤ ደግሞስ የምትጠይቂው ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይፈቀድልሻል” አላት።
7አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ልመናዬም፣ ጥያቄዬም ይህ ነው፤ 8በንጉሡ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁና የምፈልገውን ሊሰጠኝና ልመናዬንም ሊፈጽምልኝ ንጉሡን ደስ ካሠኘው፣ ንጉሡና ሐማ በማዘጋጅላቸው ግብዣ ላይ ነገ ይገኙልኝ። ከዚያም እኔ ለንጉሡ ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ።”
ሐማ በመርዶክዮስ ላይ ያወረደው ቍጣ
9ሐማ በዚያ ቀን ደስ ብሎትና መንፈሱ ረክቶ ወጣ፤ ነገር ግን መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ሲያየው ከተቀመጠበት አለመነሣቱንና በፊቱም አለመንቀጥቀጡን ሲመለከት፣ ቍጣው በመርዶክዮስ ላይ ነደደ። 10ሐማ ግን እንደ ምንም ራሱን ተቈጣጥሮ ወደ ቤቱ ሄደ።
ወዳጆቹንና ሚስቱን ዞሳራን አስጠርቶ በአንድነት ከሰበሰባቸው በኋላ፣ 11ሐማ ስለ ሀብቱ ታላቅነት፣ ስለ ልጆቹ ብዛት እንዲሁም ንጉሡ የቱን ያህል እንዳከበረው፣ ከሌሎቹም መኳንንትና ሹማምት ይበልጥ እንዴት ከፍ ከፍ እንዳደረገው እያጋነነ ነገራቸው። 12ሐማም፣ “ምን ይህ ብቻ” አለ፤ “ንግሥት አስቴር ባዘጋጀችው ግብዣ ላይ ከንጉሡ ጋራ እንድገኝ የጋበዘችው ሰው አንድ እኔ ብቻ ነኝ፤ ነገም ከንጉሡ ጋራ ጋብዛኛለች። 13ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ላይ ተቀምጦ ካየሁት ይህ ሁሉ እኔን ደስ አያሠኘኝም።”
14ሚስቱ ዞሳራና ወዳጆቹ በሙሉ፣ “ቁመቱ ዐምሳ ክንድ#5፥14 23 ሜትር ያህል ነው። የሆነ መስቀያ አስተክልና መርዶክዮስ እንዲሰቀልበት በጧት ለንጉሡ ንገረው፤ ከዚያም ደስ ብሎህ ከንጉሡ ጋራ ወደ ግብዣው ግባ” አሉት። ይህም ሐሳብ ሐማን እጅግ ደስ አሠኘው፤ መስቀያውንም አስተከለ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.