አስቴር 4:1-7
አስቴር 4:1-7 NASV
መርዶክዮስ የተደረገውን ሁሉ ባወቀ ጊዜ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ከዚያም ማቅ ለብሶ፣ በራሱ ላይ ዐመድ ነስንሶ ድምፁን ከፍ በማድረግ አምርሮ እየጮኸ ወደ ከተማዪቱ መካከል ወጣ። ማቅ የለበሰ እንዲገባ ስለማይፈቀድለት፣ የሄደው እስከ ንጉሡ በር ድረስ ብቻ ነበር። የንጉሡ ዐዋጅና ትእዛዝ በደረሰበት አውራጃ ሁሉ፣ በአይሁድ መካከል ታላቅ ሐዘን ሆነ፤ ጾሙ፤ አለቀሱ፤ ጮኹም። ብዙዎቹም ማቅና ዐመድ ላይ ተኙ። የአስቴር ደንገጡሮችና ጃንደረቦች መጥተው ስለ መርዶክዮስ በነገሯት ጊዜ፣ ንግሥቲቱ እጅግ ዐዘነች፤ እርሷም በማቁ ፈንታ የሚለብሰውን ልብስ ላከችለት፤ እርሱ ግን አልተቀበላቸውም። ከዚያም አስቴር ከንጉሡ ጃንደረቦች መካከል እርሷን እንዲያገለግል የተመደበውን ሀታክን ጠርታ፣ መርዶክዮስ ምን ችግር እንደ ገጠመውና ስለ ምንስ እንደዚህ እንደ ሆነ እንዲያጣራ ላከችው። ስለዚህ ሀታክ በንጉሡ በር ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ከተማዪቱ አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ወጣ። መርዶክዮስ የደረሰበትን ነገር ሁሉ፣ እንዲሁም ሐማ የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማግባት ቃል የገባውን የገንዘብ ልክ ጭምር ነገረው።

