ሐዋርያት ሥራ 8:26-40
ሐዋርያት ሥራ 8:26-40 NASV
የጌታም መልአክ ፊልጶስን፣ “ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ሄደ። እነሆ፤ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባለሟልና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘ። ይህም ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር። ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን፣ “ሂድ፤ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው። ፊልጶስም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ሄደ፤ ጃንደረባውም የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብብ ሰምቶ፣ “ለመሆኑ፣ የምታነብበውን ታስተውለዋለህን?” አለው። ጃንደረባውም፣ “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውላለሁ” አለው፤ እርሱም ወደ ሠረገላው ወጥቶ ዐብሮት እንዲቀመጥ ፊልጶስን ለመነው። ጃንደረባው ያነብብ የነበረው የመጽሐፍ ክፍል ይህ ነበር፤ “እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ አፉን አልከፈተም። ራሱን በማዋረዱም ፍትሕን ተነፈገ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና፣ ስለ ትውልዱ ማን ሊናገር ይችላል?” ጃንደረባውም መልሶ ፊልጶስን፣ “ነቢዩ ይህን የሚናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነው ወይስ ስለ ሌላ ሰው? እባክህ ንገረኝ” አለው። ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚሁም መጽሐፍ ክፍል ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌል ሰበከለት። በመጓዝ ላይ ሳሉም ውሃ ካለበት ስፍራ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፣ “እነሆ፤ ውሃ እዚህ አለ፤ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው። [ፊልጶስም፣ “በፍጹም ልብህ ካመንህ መጠመቅ ትችላለህ” አለው። ጃንደረባውም፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ” ሲል መለሰለት፤] ሠረገላውም እንዲቆም አዘዘ። ከዚያም ሁለቱ ዐብረው ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው። ከውሃውም በወጡ ጊዜ፣ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጥቆ ወሰደው፤ ጃንደረባውም ከዚህ በኋላ አላየውም፤ ሆኖም ደስ እያለው ጕዞውን ቀጠለ። ከዚያ በኋላ ግን ፊልጶስ በአዛጦን ታየ፤ ቂሳርያም እስኪደርስ ድረስ በሚያልፍባቸው ከተሞች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር።

