2 ተሰሎንቄ 1:3-12

2 ተሰሎንቄ 1:3-12 NASV

ወንድሞች ሆይ፤ እምነታችሁ በየጊዜው እያደገ በመሄዱና የእርስ በርስ ፍቅራችሁም እየጨመረ በመምጣቱ፣ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በሚገባ ማመስገን አለብን። ስለዚህ በደረሰባችሁ ስደትና መከራ ሁሉ በመጽናታችሁ፣ እኛ ራሳችን ስለ ትዕግሥታችሁና ስለ እምነታችሁ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንመካለን። ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ቅን መሆኑን የሚያመለክት ነው፤ ከዚህም የተነሣ መከራን ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የበቃችሁ ሆናችሁ ትቈጠራላችሁ። እግዚአብሔር ጻድቅ በመሆኑ መከራን ለሚያመጡባችሁ መከራን ይከፍላቸዋል፤ መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋራ ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ነው። በዚያ ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል። እነርሱም ከጌታ ፊትና ከኀይሉ ክብር ተወግደው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ፤ የሚቀጡትም በቅዱሳኑ ዘንድ ሊከብርና በሚያምኑበትም ሁሉ ሊገረም በሚመጣበት በዚያ ቀን ይሆናል፤ እናንተም ከሚያምኑት መካከል ናችሁ፤ ምስክርነታችንን ተቀብላችኋልና። ይህን እያሰብን አምላካችን ለጥሪው የበቃችሁ አድርጎ እንዲቈጥራችሁ፣ በጎ ለማድረግ ያላችሁን ምኞትና ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ዘወትር ስለ እናንተ እንጸልያለን። ደግሞም እንደ አምላካችንና እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ መጠን የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ ዘንድ እንዲከብርና እናንተም በርሱ እንድትከብሩ ይህን እንጸልያለን።