2 ሳሙኤል 15

15
የአቤሴሎም ዐመፅ
1ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች እንዲሁም ፊት ፊቱ የሚሮጡ ዐምሳ ሰዎች ለራሱ አዘጋጀ። 2አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ሆነ ብሎ ይቆም ነበር። ማንኛውም ባለጕዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፣ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፣ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፣ “አገልጋይህ ከአንዱ የእስራኤል ነገዶች ነው” ብሎ ይመልስለታል። 3ከዚያም አቤሴሎም፣ “ተመልከት! ጕዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ የትኛው የንጉሥ እንደራሴ ነው ታዲያ የሚያይልህ?” ይለዋል። 4ቀጠል አድርጎም፣ “ምነው ዳኛ ሆኜ በምድሪቱ ላይ በተሾምሁ አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ እየመጣ ፍትሕ እንዲያገኝ አደርገው ነበር” ይል ነበር።
5እንዲሁም ማንኛውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፣ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር። 6አቤሴሎም ፍትሕ ለማግኘት ወደ ንጉሡ የሚመጣውን እስራኤላዊ ሁሉ የሚቀርበው በዚህ መንገድ ስለ ነበር፣ የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።
7ከአራት ዓመት#15፥7 የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም፣ የሱርስቱ ቅጅና የአይሁዳዊው የታሪክ ጸሓፊ የዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ጽሑፎች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ ዕብራይስጡ ግን፣ አርባ ይላል። በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ 8እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በጌሹር ሳለሁ ‘እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደ ሆነ፣ በኬብሮን#15፥8 አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ ዕብራይስጡ ግን፣ ኬብሮን የሚለውን ቃል አይጨምርም።እግዚአብሔር እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።”
9ንጉሡም፣ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ።
10ከዚያም አቤሴሎም፣ “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፣ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር ሠራተኞችን በመላው የእስራኤል ነገዶች አሰማራ። 11ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አቤሴሎም ሄዱ፤ በእንግድነት ተጋብዘው በየዋህነት ከመሄዳቸው በቀር፣ ስለ ጕዳዩ የሚያውቁት አንዳችም ነገር አልነበረም። 12አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው የጊሎን ሰው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየጨመረ መጣ።
የዳዊት ሽሽት
13መልእክተኛም መጥቶ፣ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋራ ሆኗል” ብሎ ለዳዊት ነገረው።
14ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት ሹማምቱ ሁሉ፣ “ተነሡ እንሽሽ፤ አለዚያ አንዳችንም ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ አሁኑኑ ከዚህ መውጣት አለብን፤ ካልሆነ ገሥግሦ መጥቶ ከያዘን እኛን ያጠፋናል፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ይመታታል” አላቸው።
15የንጉሡ ሹማምትም፣ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት።
16ንጉሡ ከመላው ቤተ ሰቡ ጋራ ወጣ፤ ቤተ መንግሥቱንም እንዲጠብቁ ዐሥር ቁባቶች አስቀረ። 17ስለዚህ ንጉሡ መላውን ሕዝብ አስከትሎ ወጣ፤ ጥቂት ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቦታ ቆሙ። 18ሰዎቹ ሁሉ፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጋት ዐብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጋታውያንን ሁሉ ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ።
19ንጉሡም ጋታዊውን ኢታይን እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋራ የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሡ ከአቤሴሎም ጋራ ተቀመጥ፤ አንተ ለራስህ ከአገርህ ተወስደህ የመጣህ እንግዳ ነህ፤ 20የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋራ እንድትንከራተት ላድርግ? በል አሁንም ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ በጎነትና ታማኝነትም ከአንተ ጋራ ይሁን” አለው።
21ኢታይ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲሁም በጌታዬ በንጉሡ እምላለሁ፤ ሕይወትም ይሁን ሞት በየትም ቦታ ንጉሥ ጌታዬ የሚሆነውን ሁሉ አገልጋይህም እንደዚያው ይሆናል” ብሎ መለሰለት።
22ዳዊትም ኢታይን፣ “በል እንግዲያው ቅደምና ሂድ” አለው። ስለዚህ ጋታዊው ኢታይን ሰዎቹን ሁሉና ዐብረውት የነበሩትን ቤተ ሰቦቹን ይዞ ሄደ።
23ሕዝቡ ሁሉ በሚያልፍበትም ጊዜ ባላገሩ በሙሉ እየጮኸ አለቀሰ፤ ንጉሡም የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሻግሮ ወደ ምድረ በዳው ተጓዘ።
24ሳዶቅም በዚያ ነበር፤ ዐብረውት የነበሩትም ሌዋውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ነበር። እነርሱም የእግዚአብሔርን ታቦት ዐሳረፉ፤ አብያታርም ሕዝቡ በሙሉ ከከተማዪቱ ለቅቆ እስኪወጣ ድረስ መሥዋዕት አቀረበ#15፥24 ወይም አብያታር ሄዶ
25ከዚያም ንጉሡ ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማዪቱ ይዘህ ተመለስ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ እርሱ እኔንም መልሶ ታቦቱንና ማደሪያውን እንደ ገና ለማየት ያበቃኛል፤ 26ነገር ግን እርሱ፣ ‘ባንተ አልተደሰትሁም’ የሚል ከሆነ፣ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግብኝ፤ እኔም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።”
27እንዲሁም ንጉሡ ካህኑን ሳዶቅን እንዲህ አለው፤ “አንተ ነቢይ አይደለህምን? እንግዲህ አንተም ልጅህን አኪማአስን፣ የአብያታርን ልጅ ዮናታንን ይዘህ በሰላም ወደ ከተማዪቱ ተመለስ። አንተና አብያታር ሁለቱን ልጆቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ። 28እኔም ከአንተ ዘንድ ወሬ እስካገኝ ድረስ በምድረ በዳው በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ እቈያለሁ” 29ስለዚህ ሳዶቅና አብያታር የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ እዚያው ቈዩ።
30ዳዊት ግን እያለቀሰ የደብረ ዘይትን ተራራ ሽቅብ ወጣ፤ ራሱን ተከናንቦ፣ ባዶ እግሩን ነበር፤ ዐብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ እንደዚሁ ራሱን ተከናንቦ እያለቀሰ ሽቅብ ይወጣ ነበር። 31በዚህ ጊዜ፣ “ከአቤሴሎም ጋራ ካሤሩት መካከል አንዱ አኪጦፌል ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህን የአኪጦፌልን ምክር ወደ ከንቱነት ለውጠው” ብሎ ጸለየ።
32ዳዊትም ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክበት ወደ ተራራው ጫፍ ሲደርስ፣ አርካዊው ኩሲ ልብሱን ቀድዶ ትቢያ በራሱ ላይ ነስንሶ ሊገናኘው መጣ። 33ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፤ “ዐብረኸኝ ብትሄድ ሸክም ትሆንብኛለህ፤ 34ነገር ግን ወደ ከተማዪቱ ተመልሰህ አቤሴሎምን፣ ‘ንጉሥ ሆይ፤ አገልጋይህ እሆናለሁ፤ ቀድሞ የአባትህ አገልጋይ እንደ ነበርሁ ሁሉ፣ ዛሬም አንተን አገለግልሃለሁ’ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር በማፍረስ ትረዳኛለህ። 35ካህናቱ ሳዶቅና አብያታር እዚያው ከአንተው ጋራ ይሆኑ የለምን? ከንጉሡ ቤትም የምትሰማትን ሁሉ ንገራቸው። 36የሳዶቅ ልጅ አኪማአስና የአብያታር ልጅ ዮናታን፣ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው እዚያው ዐብረዋቸው ይገኛሉ። የምትሰማትን ሁሉ በእነርሱ ላክልኝ።”
37ስለዚህ የዳዊት ወዳጅ ኩሲ ልክ አቤሴሎም ኢየሩሳሌም በገባበት ሰዓት እዚያው ከተማ ደረሰ።

Currently Selected:

2 ሳሙኤል 15: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ