2 ነገሥት 8

8
የሱነማዪቱ ርስት ተመለሰ
1በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ፣ ልጇ ከሞት ያስነሣላትን ሴት፣ “እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ የሰባት ዓመት ራብ ስለ ወሰነ፣ ተነሺና ለጊዜው መቈየት ወደምትችዪበት ቦታ ከቤተ ሰብሽ ጋራ ሂጂ” አላት። 2ሴቲቱም ተነሥታ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነገራት አደረገች፤ ከነቤተ ሰቧም ሄዳ፣ በፍልስጥኤም ምድር ሰባት ዓመት ተቀመጠች።
3ከሰባት ዓመት በኋላም፣ ከፍልስጥኤም ምድር ተመልሳ መጣች፤ ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ አቤቱታ ለማቅረብም ወደ ንጉሡ ሄደች። 4በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው አገልጋይ ግያዝን፣ “ኤልሳዕ ያደረጋቸውን ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ እስኪ ንገረኝ” እያለው ነበር። 5ኤልሳዕ ልጇን ከሞት ያስነሣላት ሴት ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለማመልከት ወደ ንጉሡ ዘንድ የቀረበችውም፣ ኤልሳዕ የሞተውን ልጅ እንዴት እንዳስነሣ ግያዝ ለንጉሡ በሚነግርበት ወቅት ነበር።
ግያዝም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ሴቲቱ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣው ልጇም ይህ ነው” አለ። 6ንጉሡም ስለ ስለዚሁ ጕዳይ ጠየቃትና ነገረችው።
ከዚያም ንጉሡ፣ “የነበራትን ሁሉ እንዲሁም ትታ ከሄደችበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ያለውን የዕርሻዋን ሰብል በሙሉ እንድትመልስላት” ሲል አንድ ሹም አዘዘላት።
አዛሄል ቤን ሃዳድን ገደለ
7ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በዚያ ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ቤን ሃዳድ ታምሞ ነበር፤ ለንጉሡም፣ “የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቷል” ብለው ነገሩት። 8ንጉሡም አዛሄልን፣ “ገጸ በረከት ይዘህ ሂድና የእግዚአብሔርን ሰው ተገናኘው። በርሱም አማካይነት፣ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ብለህ እግዚአብሔርን ጠይቅ” አለው።
9አዛሄልም ደማስቆ ካፈራቻቸው ምርጥ ነገሮች ሁሉ የአርባ ግመል ጭነት ገጸ በረከት ይዞ ኤልሳዕን ለመገናኘት ሄደ። ሄዶም ፊቱ ቆመና፣ “የሶርያ ንጉሥ ልጅህ ቤን ሃዳድ፣ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ሲል ወደ አንተ ልኮኛል” አለው።
10ኤልሳዕም፣ “ሂድና፣ ‘መዳኑንስ በርግጥ ትድናለህ’ በለው፤ ነገር ግን#8፥10 የዕብራይስጡ ሂድና “በርግጥ አትድንም” በለው ተብሎ ሊነበብ ይችላል። እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጾልኛል” ሲል መለሰለት። 11እስኪያፍር ድረስም፣ አዛሄልን ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ሰው እንባውን አፈሰሰ።
12አዛሄልም፣ “ጌታዬ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።
ኤልሳዕም መልሶ፣ “በእስራኤላውያን ላይ የምታደርሰውን ጕዳት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ጕልማሶቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ሕፃናታቸውን በምድር ላይ ትፈጠፍጣለህ፤ ያረገዙ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትቀድዳለህ” አለው።
13አዛሄልም፣ “ለመሆኑ እንደ ውሻ የሚቈጠር አገልጋይህ ይህን ጀብዱ መፈጸም እንዴት ይችላል?” አለ።
ኤልሳዕም መልሶ፣ “መቼም አንተ በሶርያ ላይ እንደምትነግሥ እግዚአብሔር አሳይቶኛል” አለው።
14ከዚያም አዛሄል ከኤልሳዕ ዘንድ ወጥቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፤ ቤን ሃዳድም፣ “ለመሆኑ ኤልሳዕ ምን አለህ?” ሲል ጠየቀው፤ አዛሄልም፣ “በርግጥ ከበሽታህ እንደምትድን ነግሮኛል” አለው። 15በማግስቱም ግን ወፍራም ልብስ ወስዶ በውሃ ከነከረ በኋላ የንጉሡን ፊት ሸፈነው፤ ንጉሡም በዚሁ ሞተ፤ ከዚያም አዛሄል በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ይሆራም
8፥17-24 ተጓ ምብ – 2ዜና 21፥5-1021፥20
16የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐምስተኛው ዓመት፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ይሆራም በይሁዳ ነገሠ። 17እርሱ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ። 18እርሱም የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም የእስራኤል ነገሥታት የሄዱበትን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 19ይሁን እንጂ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት ሲል፣ እግዚአብሔር ይሁዳን ማጥፋት አልፈለገም፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም መብራት እንደሚሰጥ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።
20በይሆራም ዘመነ መንግሥት፣ ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ የራሱን ንጉሥ አነገሠ። 21ስለዚህም ኢዮራም ሠረገሎቹን ሁሉ አሰልፎ ወደ ጸዒር ተሻገረ። በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሠረገላ አዛዦቹን ሁሉ የከበቧቸውን ኤዶማውያንን መታ፤ ሰራዊቱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 22ኤዶም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንዳመፀ ነው፤ ልብናም በዚሁ ጊዜ ዐምፆ ነበር።
23በኢዮራም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 24ኢዮራምም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እንደ እነርሱም ሁሉ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አካዝያስም በምትኩ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ
8፥25-29 ተጓ ምብ – 2ዜና 22፥1-6
25የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ በይሁዳ ነገሠ። 26አካዝያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አንድ ዓመት ገዛ። እናቱ ጎቶልያ ትባላለች። እርሷም የእስራኤል ንጉሥ የዖምሪ የልጅ ልጅ ነበረች። 27አካዝያስ ከአክዓብ ቤተ ሰብ ጋራ በጋብቻ የተሳሰረ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
28አካዝያስም ከአክዓብ ልጅ ከኢዮራም ጋራ ሆኖ በሶርያ ንጉሥ በአዛሄል ላይ ለመዝመት ወደ ራሞት ገለዓድ ሄደ፤ ሶርያውያንም በዚያ ኢዮራምን አቈሰሉት። 29ስለዚህ ንጉሥ ኢዮራም፣ ከአዛሄል ጋራ ራማት#8፥29 በዕብራይስጡ ራማ ማለትም የራማት ሌላው መጠሪያን ይጠቀማል። ላይ ባደረገው ጦርነት ሶርያውያን ካቈሰሉት ቍስል ለመዳን ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ።
ከዚያም የአክዓብ ልጅ ኢዮራም ስለ ታመመ፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራሆም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

Currently Selected:

2 ነገሥት 8: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ