2 ነገሥት 12
12
ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን ዐደሰ
12፥1-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 24፥1-14፤ 24፥23-27
# 12 በዕብራይስጡ ጽሑፍ 12፥1-21 እንደ 12፥2-21 ብሎ ነው። 1ኢዩ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ ነገሠ፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አርባ ዓመት ገዛ። እናቱ ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች። 2ካህኑ ዮዳሄ ያስተምረው በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ። 3ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር።
4ኢዮአስ ካህናቱን እንዲህ አላቸው፤ “ከሕዝብ ቈጠራ የተገኘውንና በስእለት የገባውን እንዲሁም በራስ ፈቃድ ለእግዚአብሔር ቤት የተሰጠውን የተቀደሰ ገንዘብ በሙሉ ሰብስቡ። 5እያንዳንዱም ካህን ገንዘቡን ከገንዘብ ያዡ እጅ ይቀበል፤ እንደ አስፈላጊነቱም በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ለማደስ ይዋል።”
6ይሁን እንጂ እስከ ሃያ ሦስተኛው የኢዮአስ ዘመነ መንግሥት ካህናቱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን አላደሱም ነበር። 7ስለዚህ ንጉሡ ኢዮአስ ካህኑን ዮዳሄንና ሌሎቹን ካህናት ጠርቶ፣ “በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ያላደሳችሁት ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው፤ ቀጥሎም፣ “ከእንግዲህ ወዲያ ገንዘቡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የፈረሰውን ለማደስ ይዋል እንጂ ከገንዘብ ያዦች አትቀበሉ” አላቸው። 8ካህናቱም ከእንግዲህ ከሕዝቡ ገንዘብ ላለመሰብሰብና ቤተ መቅደሱንም ራሳቸው ላለማደስ ተስማሙ።
9ከዚያም ካህኑ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ በመክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀለት፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚያስገባው በስተቀኝ በኩል በመሠዊያው አጠገብ አኖረው። በራፉን የሚጠብቁት ካህናትም ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣውን ገንዘብ በሙሉ በሣጥኑ ውስጥ ያስገቡ ነበር። 10በሣጥኑም ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ፣ የንጉሡ ጸሓፊና ሊቀ ካህናቱ መጥተው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ ቈጥረው በየከረጢቱ በማስገባት ቋጥረው ያኖሩት ነበር። 11የገንዘቡ ልክም ተመዝኖ ከታወቀ በኋላ፣ የቤተ መቅደሱን ሥራ በኀላፊነት እንዲያሠሩ ለተመደቡት ሰዎች ገንዘቡን ያስረክቧቸዋል፤ ይህም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለሚሠሩ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ግንበኞች፣ 12ለድንጋይ ጠራቢዎችና ለድንጋይ ቅርጽ አውጭዎች የሚከፈል፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለሚታደስበት ዕንጨትና ጥርብ ድንጋይ መግዣ የሚውል ነበር።
13ለቤተ መቅደሱ ከገባው ገንዘብ ግን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግልጋሎት ለሚውሉ የብር ጽዋዎች፣ መኰስተሪያዎች፣ ድስቶች፣ መለከቶችና ወይም ለሌሎች የወርቅም ሆነ የብር ዕቃዎች መሥሪያ አልዋለም፤ 14የተከፈለው ግን የእግዚአብሔርን ቤት ለሚያድሱ ሠራተኞች ብቻ ነበር። 15ለሠራተኞቹ እንዲከፍሉ ገንዘቡ የተሰጣቸው ሰዎች ፍጹም ታማኞች በመሆናቸው ተቈጣጣሪ ማድረግ አላስፈለጋቸውም ነበር። 16ስለ በደል መሥዋዕትና ስለ ኀጢአት መሥዋዕት#12፥16 የመንጻት መሥዋዕት የሚቀርበው ገንዘብ ግን የካህናቱ በመሆኑ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይገባም ነበር።
17በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል ወጣ፤ ጋትንም አደጋ ጥሎ ያዛት። ከዚያም በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ፊቱን አዞረ። 18የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ ግን አባቶቹ የይሁዳ ነገሥታት ኢዮሣፍጥ፣ ኢዮራም፣ አካዝያስ ለእግዚአብሔር ቀድሰው የለዩአቸውን የተቀደሱ ዕቃዎች በሙሉ፣ እርሱ ራሱ የቀደሳቸው ስጦታዎች እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ ሁሉ ሰብስቦ ለሶርያ ንጉሥ ለአዛሄል ላከለት፤ አዛሄልም ከኢየሩሳሌም ተመለሰ።
19ኢዮአስ በዘመነ መንግሥቱ ያከናወነው ሌላው ተግባርና የፈጸመው ሥራ ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 20ሹማምቱም በርሱ ላይ ዐመፁበት፤ ቍልቍል ወደ ሲላ በሚወስደው መንገድ ላይ በቤት ሚሎ ገደሉት። 21ገዳዮቹ ሹማምትም የሰምዓት ልጅ ዮዛካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት ነበሩ። እርሱም ሞተ፤ እንደ አባቶቹም ሁሉ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ አሜስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.