2 ነገሥት 11

11
ጎቶልያና ኢዮአስ
11፥1-21 ተጓ ምብ – 2ዜና 22፥10–23፥21
1የአካዝያስ እናት ጎቶልያ ልጇ መሞቱን ባየች ጊዜ፣ ንጉሣውያን ቤተ ሰብ በሙሉ አጠፋች። 2የንጉሥ ኢዮራም ልጅ፣ የአካዝያስ እኅት ዮሳቤት ግን የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ሊገደሉ ከነበሩት ልዑላን መካከል ሰርቃ ወሰደችው። እንዳይገደልም ከጎቶልያ በመደበቅ እርሱንና ሞግዚቱን በአንድ እልፍኝ ሸሸገቻቸው። 3እርሱም ጎቶልያ ምድሪቱን በምትገዛበት ጊዜ ከሞግዚቱ ጋራ በእግዚአብሔር ቤት ተደብቆ ስድስት ዓመት ኖረ።
4በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ ካራውያንንና ዘብ ጠባቂዎቹን የሚያዝዙትን የመቶ አለቆች እርሱ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲመጡ አደረገ። ከእነርሱም ጋራ ቃል ኪዳን በማድረግ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አስማላቸው፤ ከዚያም የንጉሡን ልጅ አሳያቸው። 5እንዲህም ሲል አዘዛቸው፤ “እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሦስት ምድብ ሆናችሁ በሰንበት ዕለት ዘብ ከምትጠብቁት መካከል አንዱ እጅ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቅ፤ 6ሌላው ከሦስት እጅ አንዱ የሱርን በር ይጠብቅ፤ የቀረው ሌላው አንድ ሦስተኛው እጅ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ተራ ገብቶ ከሚጠብቀው ከዘብ ጥበቃው ኋላ ያለውን በር ይጠብቅ። 7እናንተ እንደተለመደው በሰንበት ዕለት ከዘብ ጥበቃ ነጻ የምትሆኑት ሁለት ሦስተኛው እጅ ግን ንጉሡ ያለበትን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ጠብቁ። 8እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ ይዞ በንጉሡ ዙሪያ ሁኑ፤ የሚቀርባችሁ ማንም ሰው ቢኖር#11፥8 ወይም፣ ወደ ቅጥራችሁ የሚደርስ ቢኖር ግን ይገደል። ንጉሡ በሚወጣበትም ሆነ በሚገባበት ጊዜ ሁሉ ዐብራችሁት ሁኑ።”
9የመቶ አለቆቹም ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዘው አደረጉ፤ እያንዳንዳቸውም በሰንበት ዕለት ለዘብ ጥበቃ የሚገቡትንና ከዘብ ጥበቃ የሚወጡትን ጭፍሮቻቸውን ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ። 10ካህኑም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊትን ጦሮችና ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው። 11ወታደሮቹም እያንዳንዱ መሣሪያውን በእጁ ይዞ፣ ከቤተ መቅደሱ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ ቆሙ።
12ዮዳሄም የንጉሡን ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነለት፤ ኪዳኑንም ሰጠው፤ መንገሡን ዐወጁ፤ ቀብተውም አነገሡት። ከዚያም ሕዝቡ፣ “ንጉሡ ሺሕ ዓመት ይንገሥ” እያሉ በማጨብጨብ ደስታቸውን ከፍ ባለ ድምፅ ገለጹ።
13ጎቶልያም የሰራዊቱንና የሕዝቡን ጩኸት ስትሰማ፣ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደች። 14እነሆ፤ በወጉ መሠረት ንጉሡ በዐምዱ አጠገብ ቆሞ፣ ሹማምቱና መለከት ነፊዎቹ ከአጠገቡ ሆነው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ይፈነጥዝ፣ መለከትም ይነፋ ነበር። ጎቶልያም ልብሷን ቀድዳ፣ “ይህ ክሕደት ነው! ክሕደት ነው!” ብላ ጮኸች።
15ካህኑ ዮዳሄም የወታደሮች አዛዥ ወደሆኑት የመቶ አለቆች፣ “በረድፍ በተሰለፉት ጭፍሮች መካከል አውጧት፤#11፥15 ወይም፣ ከቅጥራችሁ መካከል የሚከተላትንም ሁሉ በሰይፍ ግደሉት” ሲል አዘዘ፤ ይህ የሆነውም ካህኑ አስቀድሞ፣ “በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገደል የለባትም” በማለቱ ነበር። 16ስለዚህ ፈረሶች ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚገቡበት መንገድ ስትደርስ ያዟት፤ በዚያም ተገደለች።
17ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን እንዲመሠረት አደረገ፤ እንደዚሁም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን መሠረተ። 18ከዚያም የአገሩ ሕዝብ ሁሉ ሄደው የበኣልን ቤተ ጣዖት አፈራረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን ሰባበሩ፤ የበኣልን ካህን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት።
ካህኑ ዮዳሄም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚጠብቁ ዘበኞችን መደበ። 19ከዚያም መቶ አለቆቹን፣ ካራውያንንና ዘበኞቹን እንዲሁም የአገሩን ሕዝብ በሙሉ በመያዝ ሁሉም በአንድነት ሆነው፣ ንጉሡን ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወስደው በዘብ ጠባቂዎች ቅጥር በር በኩል ታች ወዳለው ቤተ መንግሥት ይዘውት ገቡ፤ ንጉሡም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ 20የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ተደሰተ፤ ጎቶልያ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሰይፍ ተገድላ ስለ ነበር፣ ከተማዪቱ ጸጥ አለች።
21ኢዮአስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር።

Currently Selected:

2 ነገሥት 11: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ