ዘፍጥረት 43

43
የዮሴፍ ወንድሞች ዳግመኛ ወደ ግብጽ መሄዳቸው
1ራቡ አሁንም በምድሪቱ ላይ እንደ ጸና ነበር፤ 2ከግብጽ ያመጡትንም እህል በልተው ከጨረሱ በኋላ፣ አባታቸው “እስኪ እንደ ገና ወርዳችሁ፣ ጥቂት እህል ሸምቱልን” አላቸው።
3ይሁዳ ግን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎ በጥብቅ አስጠንቅቆናል፤ 4ወንድማችን ከእኛ ጋራ እንዲወርድ ከፈቀድህ ወደዚያ ሄደን እህል እንሸምትልሃለን፤ 5እርሱን የማትልከው ከሆነ ግን እኛም ወደዚያ አንወርድም፤ ያም ሰው፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎናል።”
6እስራኤልም፣ “ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለዚያ ሰው በመንገር ለምን ይህን ችግር እንዲደርስብኝ አደረጋችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
7እነርሱም፣ “ሰውየው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተ ሰባችን አጥብቆ ጠየቀን፤ እንደ ገናም ‘አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ?’ ሲል ጠየቀን። እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው። ታዲያ፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደዚህ እንድትመጡ’ እንደሚል እንዴት ማወቅ እንችል ነበር?” ብለው መለሱለት።
8ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው “ልጁን ከእኔ ጋራ ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፤ ይህ ከሆነ፣ አንተም፣ እኛም፣ ልጆቻችንም አንሞትም፤ እንተርፋለን። 9ስለ ልጁ ደኅንነት እኔ ራሴ ኀላፊ ነኝ፤ ስለ እርሱም በግል ተጠያቂ እሆናለሁ፤ እርሱንም በደኅና መልሼ ባላመጣውና እዚህ በፊትህ ባላቆመው ለዘላለም በደለኛው እኔ ልሁን። 10ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ፣ እስካሁን ሁለት ጊዜ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።”
11ከዚህ በኋላ አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፤ “ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህን አድርጉ፤ ምድሪቱ ከምታፈራው ምርጥ ነገሮች ጥቂት በለሳን፣ ጥቂት ማር፣ ሽቱ፣ ከርቤ፣ ተምርና አልሙን በየስልቻችሁ ይዛችሁ ለዚያ ሰው እጅ መንሻ ውሰዱለት። 12በየስልቾቻችሁ አፍ ላይ የተገኘውን ብር መመለስ ስላለባችሁ፣ ዕጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ ያ በየስልቾቻችሁ ውስጥ የተገኘው ብር ምናልባት በስሕተት የመጣ ሊሆን ይችላል። 13ወንድማችሁንም ይዛችሁ ወደ ሰውየው በቶሎ ሂዱ። 14ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ይዛችሁ ለመመለስ እንድትችሉ ሁሉን ቻይ#43፥14 ዕብራይስጡ ኤልሻዳይ ይላል። አምላክ በምሕረቱ የዚያን ሰው ልብ ያራራላችሁ። እንግዲህ ልጆቼንም ባጣ ምን አደርጋለሁ፤ ያመጣውን እቀበላለሁ።”
15ሰዎቹም እጅ መንሻውን፣ የብሩን ዕጥፍ እንዲሁም ብንያምን ይዘው ተነሡ፤ ወደ ግብጽም በፍጥነት ወረዱ፤ ዮሴፍም ፊት ቀረቡ። 16ዮሴፍ ብንያምን ከወንድሞቹ ጋራ ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ፣ “እነዚህን ሰዎች ወደ ቤት ይዘሃቸው ሂድ፤ ዛሬ ቀትር ላይ ዐብረውኝ ስለሚበሉ ፍሪዳ ተጥሎ ምሳ ይዘጋጅ” አለው።
17አዛዡም ዮሴፍ የነገረውን አደረገ፤ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው። 18ሰዎቹም ወደ ዮሴፍ ቤት በመወሰዳቸው ፈሩ፤ እነርሱም፣ “ወደዚህ የመጣነው፣ ቀደም ሲል እዚህ መጥተን ስንመለስ በየስልቾቻችን ውስጥ ተመልሶ በተጨመረው ብር ሰበብ ነው። ሰውየው ጥቃት ሊፈጽምብን፣ አስገድዶ ባሮቹ ሊያደርገንና አህዮቻችንን ሊቀማን ይፈልጋል” ብለው ሠጉ።
19ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥ ቀርበው፣ በቤቱ መግቢያ ላይ አነጋገሩት፤ 20“እንዲህም አሉት፤ ጌታችን ሆይ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እህል ለመሸመት ወደዚህ መጥተን ነበር፤ 21ነገር ግን ለዐዳር በሰፈርንበት ቦታ የየስልቾቻችንን አፍ ስንከፍት፣ እያንዳንዳችን በስልቾቻችን አፍ ላይ፣ ብራችንን ሙሉውን አገኘነው። ገንዘቡንም ይኸው መልሰን ይዘን መጥተናል። 22አሁንም እህል መሸመቻ የሚሆነን ተጨማሪ ብር ይዘን መጥተናል፤ ያኔ ገንዘቡን በየስልቾቻችን ውስጥ ማን መልሶ እንዳስቀመጠው ግን አናውቅም” አሉት።
23የቤቱ አዛዥም፣ “አይዟችሁ አትፍሩ፤ በየስልቾቻችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ገንዘብ የሰጣችሁ የእናንተም የአባቶቻችሁም አምላክ ነው፤ እኔ እንደ ሆንሁ ብሩን ተቀብያለሁ” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ አገናኛቸው።
24የቤቱ አዛዥ ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገብቶ እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አቀረበላቸው፤ ለአህዮቻቸውም የሚበሉት ገፈራ ሰጣቸው። 25ምሳ በዚያ እንደሚበሉ ተነግሯቸው ስለ ነበር፣ ዮሴፍ በቀትር ከመግባቱ በፊት እጅ መንሻዎቻቸውን ለማበርከት ተዘጋጁ።
26ዮሴፍም ወደ ቤቱ ሲገባ ያመጧቸውን እጅ መንሻዎች አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት። 27ዮሴፍም ስለ ደኅንነታቸው ጠየቃቸው፤ ከዚያም “ሽማግሌ አባት እንዳላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ደኅና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?” አላቸው።
28እነርሱም መልሰው፣ “አገልጋይህ አባታችን አሁንም በሕይወት አለ፤ ደኅና ነው” በማለት ወደ መሬት ዝቅ ብለው በአክብሮት እጅ ነሡት።
29ዮሴፍ በዐይኑ ሲቃኝ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየና፣ “ያ የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ብንያምንም፣ “ልጄ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለው። 30ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ በጥልቅ ስለ ተነካ፣ ፈጥኖ ከፊታቸው ገለል አለ፤ ሰወር ያለ ቦታም ፈልጎ፣ ዕልፍኙ ውስጥ አለቀሰ።
31ፊቱን ከታጠበ በኋላ ተመልሶ፣ ስሜቱን በመቈጣጠር፣ “ማእድ ይቅረብ” አለ።
32ለዮሴፍ ለብቻው ቀረበለት፤ ለወንድሞቹም ለብቻቸው ቀረበላቸው፤ እንዲሁም ከርሱ ጋራ ለሚበሉት ግብጻውያን ደግሞ ሌላ ገበታ ቀረበላቸው፤ ምክንያቱም ግብጻውያን ከዕብራውያን ጋራ ዐብሮ መመገብን እንደ ጸያፍ ይቈጥሩት ነበር። 33ወንድማማቾቹ ከበኵሩ እስከ ታናሹ እንደየዕድሜያቸው በዮሴፍ ፊት በተርታ ተቀምጠው ነበር፤ በመገረምም እርስ በርሳቸው ተያዩ። 34ከዮሴፍ ገበታ ላይ እየተነሣ ለእያንዳንዳቸው ምግብ ሲቀርብ፣ የብንያም ድርሻ ከሌሎቹ ዐምስት ዕጥፍ ነበር። እነርሱም እንዲህ ባለ ሁኔታ ዐብረውት ተደሰቱ፤ እስኪረኩም ጠጡ።

선택된 구절:

ዘፍጥረት 43: NASV

하이라이트

복사

비교

공유

None

모든 기기에 하이라이트를 저장하고 싶으신가요? 회원가입 혹은 로그인하세요

ዘፍጥረት 43 동영상