ዘፍጥረት 41

41
የፈርዖን ሕልም
1ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለመ፤ በሕልሙም፣ በአባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ 2እነሆ መልካቸው ያማረ፣ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር። 3ቀጥሎም መልካቸው የከፋ ዐጥንታቸው የወጣ፣ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ። 4እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፣ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ሰባት ላሞች ሲውጧቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ።
5ፈርዖንም እንደ ገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፣ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፣ ፍሬአቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ። 6ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ። 7የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፣ ፍሬአቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጧቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር።
8በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብጽ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፤ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጕምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም።
9በዚያ ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ። 10በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር። 11ሁለታችንም በአንዲት ሌሊት የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የየራሱ ትርጕም ነበረው። 12በዚያ ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋራ እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፣ ፍችውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጐመልን፤ 13ነገሩም ልክ እርሱ እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ#41፥13 ወይም ተወጋ።”
14ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጕሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ።
15ፈርዖንም ዮሴፍን፣ “ሕልም አይቼ ነበር፤ ሕልሜን ሊተረጕምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፤ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው።
16ዮሴፍም ፈርዖንን፣ “እኔ የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለፈርዖን የሚሻውን ትርጕም ይሰጠዋል” አለው።
17ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “በሕልሜ በአባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። 18ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው ያማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲበሉ አየሁ። 19ከእነርሱም በኋላ፣ ዐቅመ ደካማ፣ መልካቸው እጅግ የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብጽ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም። 20ዐጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን፣ ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጧቸው። 21ከዋጧቸውም በኋላ፣ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደ ዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ።
22“እንደዚሁም፣ በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ፍሬአቸው የፋፋና ያማሩ ሰባት እሸት ዛላዎች ወጥተው አየሁ። 23ቀጥሎም በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የቀጨጩና የደረቁ ሌሎች ሰባት ዛላዎች ወጡ። 24የቀጨጩት የእሸት ዛላዎችም ሰባቱን ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጧቸው፤ ይህንኑም ለአስማተኞች ነገርሁ፤ ነገር ግን ማንም ሊፈታው አልቻለም።”
25ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዐይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል። 26ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፣ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው። 27ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው።
28“አስቀድሜ ለፈርዖን እንደ ተናገርሁት፣ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል። 29በመላው የግብጽ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። 30ከዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጐዳት፣ በግብጽ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም። 31ከጥጋቡ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፣ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል። 32ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለ ሆነ ነው፤ ይህንም እግዚአብሔር በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል።
33“እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፣ በመላው የግብጽ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም። 34እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፣ አንድ ዐምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኀላፊዎችን ይሹም። 35እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ። 36የሚከማቸው እህል፣ ወደ ፊት በግብጽ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።”
37ዕቅዱንም ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት። 38ፈርዖንም፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ#41፥38 ወይም የአማልክት መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው።
39ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፣ እንደ አንተ ያለ አስተዋይና ብልኅ ሰው የለም። 40አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።”
ዮሴፍ በግብጽ ተሾመ
41ከዚያም፣ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “በመላዪቱ የግብጽ ምድር ላይ ኀላፊ አድርጌሃለሁ” አለው። 42ፈርዖንም ባለማኅተሙን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ በዮሴፍ ጣት ላይ አደረገው፤ እንዲሁም ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በዐንገቱም የወርቅ ሐብል አጠለቀለት። 43በማዕርግ ከርሱ ሁለተኛ ሰው አድርጎ፣ በሠረገላ ላይ አስቀመጠው።#41፥43 ወይም በማዕርግ ሁለተኛ በሆነው የርሱ ሠረገላ ላይ፤ ወይም በሁለተኛ ሠረገላው ላይ ሰዎችም በፊቱ፣ “እጅ ንሡ#41፥43 ወይም ስገዱ” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ሾመው።
44ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም በመላዪቱ ግብጽ ያላንተ ትእዛዝ እጁንም ሆነ እግሩን ልውስ የሚያደርግ አይኖርም” አለው። 45ፈርዖንም ዮሴፍን ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ስም አወጣለት። እንዲሁም የሄልዮቱ ኦን#41፥45 በቍ 50 ላይ ያለውን ጨምሮ ሆልዮፓሊስን ያመለክታል። ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በመላዪቱ የግብጽ ምድር ተዘዋወረ።
46ዮሴፍ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን ማገልገል ሲጀምር፣ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ የግብጽን ምድር በሙሉ ዞረ። 47በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ ሰብል ሰጠች። 48በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመታት፣ ዮሴፍ በግብጽ አገር የተገኘውን ምርት ሰብስቦ በየከተሞቹ አከማቸ፤ በእያንዳንዱ ከተማ ከየአቅራቢያው የተመረተውን እህል እንዲከማች አደረገ። 49ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ የሚሆን የእህል ሰብል አከማቸ፤ ሰብሉ እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ልኩን መስፈርና መመዝገብ አልቻለም ነበር።
50ሰባቱ የራብ ዓመታት ከመምጣቱ በፊት፣ የሄልዮቱ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት ለዮሴፍ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 51ዮሴፍም፣ “እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ፣ የአባቴንም ቤት እንድረሳ አድርጎኛል” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ምናሴ#41፥51 ምናሴ የሚለው ቃል መርሳት የሚል ትርጕም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የወጣ ሲሆን፣ ከዚሁ ቃል ጋራ አንድ ዐይነት ድምፅ አለው። አለው። 52እንደዚሁም፣ “መከራ በተቀበልሁበት ምድር እግዚአብሔር ፍሬያማ አደረገኝ” ሲል ሁለተኛ ልጁን ኤፍሬም#41፥52 ኤፍሬም የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ዕጥፍ ፍሬያማ የሚል ትርጕም ካለው ቃል ጋራ አንድ ዐይነት ድምፅ አለው። አለው።
53በግብጽ ምድር የነበረው ሰባቱ የጥጋብ ዘመን ዐለፈና 54ዮሴፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረው የሰባቱ ዓመት የራብ ዘመን ጀመረ። ሌሎች አገሮች ሁሉ ሲራቡ፣ በመላው የግብጽ ምድር ግን ምግብ ነበር። 55ራቡ በመላው የግብጽ ምድር መስፋፋት ሲጀምር፣ ሕዝቡ ምግብ ይሰጠን በማለት ወደ ፈርዖን ጮኸ። ፈርዖንም ግብጻውያኑን፣ “ወደ ዮሴፍ ሂዱና የሚላችሁን አድርጉ” አላቸው።
56ራቡ በአገሩ ላይ እየተስፋፋ ስለ ሄደ፣ ዮሴፍ ጐተራዎቹን ከፍቶ እህሉ ለግብጻውያን እንዲሸጥ አደረገ፤ ምክንያቱም ራቡ በመላዪቱ ግብጽ ጸንቶ ነበር። 57ራቡ በመላው ዓለም ጸንቶ ስለ ነበር፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ ከዮሴፍ ዘንድ እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ምድር መጡ።

선택된 구절:

ዘፍጥረት 41: NASV

하이라이트

복사

비교

공유

None

모든 기기에 하이라이트를 저장하고 싶으신가요? 회원가입 혹은 로그인하세요

ዘፍጥረት 41 동영상