ሮሜ 4:18-21 - ሁሉንም ስሪቶች ያወዳድሩ
ሮሜ 4:18-21 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
“ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ ለርሱ በተነገረው መሠረት፣ ምንም ተስፋ በሌለበት፣ አብርሃም በተስፋ አምኖ የብዙ ሕዝብ አባት ሆነ። እርሱ የመቶ ዓመት ሰው ሆኖ ሳለ፣ የራሱም ሰውነት ሆነ የሣራ ማሕፀን ምዉት እንደ ነበረ እያወቀ በእምነቱ አልደከመም። ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤ እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር።
ሮሜ 4:18-21 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
አብርሃም ዘርህ እጅግ ይበዛል ተብሎ በተነገረው መሠረት የብዙ ሕዝብ አባት እንደሚሆን ያመነውና ተስፋ ያደረገው ምንም ተስፋ በማይጣልበት ነገር ነው። ዕድሜው መቶ ዓመት ያኽል ስለ ነበረ በሥጋው መድከም እንደ ሞተ በመሆን ምክንያት መውለድ እንደማይችልና ሣራም መኻንና ያረጀች በመሆንዋ መውለድ እንደማትችል ቢያውቅም በእምነቱ ደካማ አልሆነም። በእምነቱ ብርቱ ሆኖ ለእግዚአብሔር ክብር ሰጠ እንጂ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ ባለማመን ከቶ አልተጠራጠረም። እግዚአብሔር የሰጠውንም ተስፋ የሚፈጽም መሆኑን በሙሉ ልብ ያምን ነበር።
ሮሜ 4:18-21 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
አብርሃም “ዘርህ እንዲሁ ይሆናል” ብሎ እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠው ተስፋ ባልነበረ ጊዜ የብዙዎች አሕዛብ አባት እንደሚሆን አመነ። አብርሃም የመቶ ዓመት ሽማግሌ ስለሆነ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሣራ ማኅፀን ምውት መሆኑን እያየ በእምነት አልተጠራጠረም። እግዚአብሔር ያናገረለትንም ተስፋ ይቀራል ብሎ አልተጠራጠረም፤ በእምነት ጸና እንጂ፤ ለእግዚአብሔርም ክብርን ሰጠ። እግዚአብሔርም የሰጠውን ተስፋ ሊያደርግለት እንደሚችል በፍጹም ልቡ አመነ።
ሮሜ 4:18-21 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ። የመቶ ዓመትም ሽማግሌ ስለ ሆነ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሳራ ማኅፀን ምውት መሆኑን በእምነቱ ሳይደክም ተመለከተ፤ ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም።
ሮሜ 4:18-21 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
“ዘርህም እንዲሁ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተነገረው፥ ተስፋ በሌለበት የብዙ ሕዝቦች አባት እንደሚሆን በተስፋ አመነ። መቶ ዓመት ሆኖት ሳለ ምውት የሆነውን የራሱን አካልና የሳራ ማኅፀን ምውት መሆን አስቦ በእምነት አልደከመም፤ ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ በእምነት በረታ እንጂ፤ እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ አልተጠራጠረም። የሰጠውንም ተስፋ እንደሚፈጽም ጽኑ እምነት ነበረው።