ቲቶ 1:5-10

ቲቶ 1:5-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አንተን በቀርጤስ የተውኩበት ምክንያት ያልተስተካከለውን እንድታስተካክልና ባዘዝኩህም መሠረት የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን በየከተማው እንድትሾም ነው። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሆነ፥ ስድ በመሆንና ባለመታዘዝ ምክንያት የማይወቀሱ አማኞች ልጆች ያሉት ሰው መሆን ይገባዋል። ኤጲስ ቆጶስ (የቤተ ክርስቲያን መሪ) የእግዚአብሔርን ሥራ በዐደራ የተቀበለ ስለ ሆነ የማይነቀፍ መሆን አለበት፤ እንዲሁም የማይኰራ፥ በቶሎ የማይቈጣ፥ የማይሰክር፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ለገንዘብ የማይስገበገብ መሆን አለበት። ይልቅስ እንግዳ ተቀባይ፥ መልካም የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ራሱን የሚቈጣጠር፥ ትክክለኛ፥ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ፥ በመጠን የሚኖር ይሁን። እውነተኛውን ትምህርት በማስተማር ለመምከርና ለተቃዋሚዎችም መልስ ለመስጠት እንዲችል በተማረው መሠረት በአስተማማኝ ቃል ይጽና። ብዙ ሰዎች፥ ይልቁንም ከአይሁድ ወገን የሆኑ የግዝረትን ሥርዓት የሚከተሉ፥ የማይታዘዙ፥ በከንቱ የሚለፈልፉና የሚያታልሉ አሉ።