መዝሙር 9:1-10
መዝሙር 9:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ ታምራትህንም ሁሉ እናገራለሁ። በአንተ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ። ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው በተመለሱ ጊዜ፥ ይታመሙ፥ ከፊትህም ይጥፉ። ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ የጽድቅ ፈራጅ ሆይ፥ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ። አሕዛብን ገሠጽህ፥ ዝንጉዎችም ጠፉ፥ ስማቸውንም ለዘለዓለም ደመሰስህ። ጠላቶች በጦር ለዘለዓለም ጠፉ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረስህ፥ ዝክራቸውንም በአንድነት ታጠፋለህ። እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም ይኖራል፥ ዙፋኑንም ለመፍረድ አዘጋጀ፤ እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይዳኛታል። አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል። እግዚአብሔርም ለድሆች መጠጊያ ሆናቸው፥ እርሱም በመከራቸው ጊዜ ረዳታቸው ነው። ስምህን የሚወዱ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ፥ አቤቱ፥ የሚሹህን አትተዋቸውምና።
መዝሙር 9:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤ ስለ ድንቅ ሥራዎችህም ሁሉ እናገራለሁ። በአንተ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፤ ስምህን በመዝሙር እወድሳለሁ። ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፣ ተሰነካክለው ከፊትህ ይጠፋሉ፤ ፍርዴም ጕዳዬም በአንተ እጅ ናቸውና፤ ቅን ፍርድ እየሰጠህ በዙፋንህ ላይ ተቀምጠሃል። ሕዝቦችን ገሠጽህ፤ ክፉዎችንም አጠፋህ፤ ስማቸውንም እስከ ወዲያኛው ደመሰስህ። ጠላቶች ለዘላለም ጠፉ፤ ከተሞቻቸውንም ገለባበጥሃቸው፤ መታሰቢያቸውም ተደምስሷል። እግዚአብሔር ግን ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ነው፤ መንበሩንም ለፍርድ አጽንቷል። ዓለምን በጽድቅ ይዳኛል፤ ሕዝቦችንም በፍትሕ ይገዛል። እግዚአብሔር ለተጨቈኑት ዐምባ ነው፤ በመከራም ጊዜ መጠጊያ ይሆናቸዋል። ስምህን የሚያውቁ ይታመኑብሃል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚሹህን አትተዋቸውምና።
መዝሙር 9:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! በሙሉ ልቤ አመሰግንሃለሁ፤ ያደረግኸውንም ድንቅ ነገር ሁሉ እናገራለሁ! በአንተ ደስ ይለኛል፤ ሐሴትም አደርጋለሁ፤ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ለስምህ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ። አንተ በምትገለጥበት ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላ ይመለሳሉ፤ ተሰናክለውም ከፊትህ ይጠፋሉ። በዙፋንህ ላይ ተቀምጠህ ትክክለኛ ፍርድን ፈራጅ ነህ። የእኔንም ጉዳይ በማየት መብቴን ጠብቀህ በቅን ትፈርድልኛለህ። አሕዛብን ገሠጽክ፤ ክፉዎችንም አጠፋህ፤ ስማቸውንም ለዘለዓለም ደመሰስህ። ጠላቶቻችን ለዘለዓለም ጠፍተዋል፤ ከተሞቻቸውንም ደምስሰሃል፤ መታሰቢያቸውም ጠፍቶአል። እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም ንጉሥ ሆኖ ይኖራል፤ ዙፋኑንም ለፍርድ አዘጋጅቶአል። ዓለምን በፍትሕ ያስተዳድራል፤ ሕዝቦችንም በትክክል ይዳኛል። እግዚአብሔር ለተጨቈኑት መጠጊያ ነው፤ በመከራ ጊዜም መከላከያ አምባ ነው። አምላክ ሆይ! በአንተ የሚተማመኑትን ሁሉ ስለማትተዋቸው ስምህን የሚያውቁ ሁሉ ይተማመኑብሃል።
መዝሙር 9:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ በሙሉ ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ። እደሰታለሁ፥ በአንተም ሐሤትን አደርጋለሁ፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ። ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፥ ይሰናከላሉ ከፊትህም ይጠፋሉ። ትክክለኛ ፍርድና ዳኝነት አድርገህልኛልና፥ በጽድቅ እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ። አሕዛብን ገሠጽህ፥ ክፉዎችንም አጠፋህ፥ ስማቸውንም ለዘለዓለም ደመሰስህ። ጠላቶች በጦር ለዘለዓለም ጠፉ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረስህ፥ ዝክራቸውም ጠፋ። ጌታ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፥ ዙፋኑንም ለመፍረድ አዘጋጀ፥ እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል፥ አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል። ጌታ ለተጨቆኑ መጠጊያ ይሁናቸው፥ በመከራም ጊዜ መሸሸጊያ ይሁንላቸው።


