መዝሙር 20:1-9
መዝሙር 20:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ በኀይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፤ በማዳንህም እጅግ ሐሤትን ያደርጋል። የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው፥ የከንፈሮቹንም ልመና አልከለከልኸውም። በበጎ በረከት ደርሰህለታልና፤ ከክቡር ዕንቍ የሆነ ዘውድንም በራሱ ላይ አኖርህ። ሕይወትን ለመነህ፥ ሰጠኸውም፥ ለረዥም ዘመን ለዘለዓለሙ። በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው፤ ክብርንና ምስጋናን ጨመርህለት። የዘለዓለም በረከትን ሰጥተኸዋልና፥ በፊትህም ደስታ ደስ ታሰኘዋለህ። ንጉሥ በእግዚአብሔር ተማምኖአልና፥ በልዑልም ምሕረት አይናወጥም። እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታግኛቸው፥ ቀኝህም የሚጠሉህን ሁሉ ታግኛቸው። ፊትህ በተቈጣ ጊዜ እንደ እሳት እቶን አድርጋቸው፤ አቤቱ፥ በቍጣህ አውካቸው፥ እሳትም ትብላቸው።
መዝሙር 20:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር በጭንቅ ቀን ይስማህ፤ የያዕቆብም አምላክ ስም ይጠብቅህ። ከመቅደሱ ረድኤት ይላክልህ፤ ከጽዮንም ደግፎ ይያዝህ። ቍርባንህን ሁሉ ያስብልህ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህን ይቀበልልህ። ሴላ የልብህን መሻት ይስጥህ፤ ዕቅድህን ሁሉ ያከናውንልህ። በአንተ ድል ደስ ይበለን፤ በአምላካችን ስም አርማችንን ከፍ እናደርጋለን። እግዚአብሔር የለመንኸውን ሁሉ ይፈጽምልህ። እግዚአብሔር፣ የቀባውን እንደሚያድን አሁን ዐወቅሁ። የማዳን ኀይል ባለው ቀኝ እጁ፣ ከተቀደሰው ሰማይ ይመልስለታል። እነዚህ በሠረገላ፣ እነዚያ በፈረስ ይመካሉ፤ እኛ ግን ትምክሕታችን የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም ነው። እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፤ እኛ ግን ተነሣን፤ ጸንተንም ቆምን። እግዚአብሔር ሆይ፤ ንጉሥን አድን፤ እኛም በጠራንህ ቀን ስማን።
መዝሙር 20:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በችግር ቀን እግዚአብሔር ጸሎትህን ይስማ! የያዕቆብ አምላክም ስም ይጠብቅህ! ከመቅደሱ ርዳታውን ይላክልህ፤ ከጽዮን ተራራም ይደግፍህ። መባህን ሁሉ ይቀበልልህ፤ በመሥዋዕትህም ደስ ይበለው። የልብህን ምኞት ይስጥህ፤ ሐሳብህን ሁሉ ይፈጽምልህ፤ ድል በማድረግህ እልል እንላለን፤ በአምላካችንም ስም ዓርማችንን ከፍ እናደርጋለን፤ እግዚአብሔር ልመናህን ሁሉ ይፈጽምልህ። እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሠውን እንደሚረዳ አሁን ዐውቃለሁ፤ በቀኝ እጁ ታላቅ ድልን በማቀዳጀት ከተቀደሰው ቦታ ከሰማይ ለጸሎቱ መልስ ይሰጠዋል። አንዳንዶች በጦር ሠረገሎቻቸው፥ ሌሎችም በፈረሶቻቸው ይመካሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ኀይል እንታመናለን። እነርሱ ተሰናክለው ይወድቃሉ፤ እኛ ግን እንነሣለን፤ ጸንተንም እንቆማለን። አምላክ ሆይ! ንጉሡን ከጠላቶቹ እጅ አድነው፤ እኛም በምንጠራህ ጊዜ ስማን።
መዝሙር 20:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በመከራ ቀን ጌታ ይስማህ፥ የያዕቆብ አምላክ ስም ያቁምህ። ከመቅደሱ ረድኤትን ይላክልህ፥ ከጽዮንም ይደግፍህ። መባዎችህን ሁሉ ያስብልህ፥ የሚቃጠል መሥዋዕትህን ያለምልምልህ። እንደ ልብህ ምኞት ይስጥህ ፈቃድህንም ሁሉ ይፈጽምልህ። በማዳንህ ደስ ይለናል፥ በአምላካችን ስም ከፍ ከፍ እንላለን፥ ልመናህን ሁሉ ጌታ ይፈጽምልህ። ጌታ የቀባውን እንዳዳነው ዛሬ አወቅሁ፥ ከሰማይ መቅደሱ ይመልስለታል፥ በቀኙ ብርታት ማዳን አለና። እነኚህ በሠረገላ እነዚያም በፈረስ ይታመናሉ፥ እኛ ግን በአምላካችን በጌታ ስም ከፍ ከፍ እንላለን። እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፥ እኛ ግን ተነሣን፥ ጸንተንም ቆምን።