ነህምያ 5:6-8
ነህምያ 5:6-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ዐዘንሁ። በልቤም አሰብሁ፤ ታላላቆቹንና ሹሞቹንም፥ “ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ” ብዬ ተጣላኋቸው፤ ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው። እኔም፥ “ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን፤ እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን?” አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፤ መልስም አላገኙም።
ነህምያ 5:6-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እኔም ጩኸታቸውንና እነዚህን አቤቱታዎች በሰማሁ ጊዜ፣ እጅግ ተቈጣሁ፤ ከዚያም ነገሩን በሐሳቤ ካወጣሁ ካወረድሁ በኋላ፣ መኳንንቱንና ሹማምቱን ገሠጽኋቸው፤ “ከገዛ አገራችሁ ሰዎች ላይ እንዴት ዐራጣ ትበላላችሁ” አልኋቸውም። ስለዚህ ከእነርሱ ጋራ ለመነጋገር ታላቅ ስብሰባ ጠራሁ፤ “ለአሕዛብ ተሽጠው የነበሩትን አይሁድ ወንድሞቻችንን በተቻለን ሁሉ ተቤዥተናቸዋል፤ አሁንም እናንተ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁ፤ ይህም መልሰን እንድንቤዣቸው ለማድረግ ብቻ ነው!” አልኋቸው፤ እነርሱም የሚመልሱት አልነበራቸውምና ዝም አሉ።
ነህምያ 5:6-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቈጣሁ። በልቤም አሰብሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም፦ ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ ብዬ ተጣላኋቸው፥ ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው። እኔም፦ ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን፥ እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን? አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፥ መልስም አላገኙም።
ነህምያ 5:6-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እኔም አቤቱታቸውን በሰማሁ ጊዜ ተቈጣሁ፤ ላደርገው የሚገባኝንም በልቤ ወስኜ የሕዝቡ መሪዎች የሆኑትን ባለሥልጣኖች “እናንተ እኮ የገዛ ወንድሞቻችሁን በመጨቈን አራጣ ታስከፍላላችሁ!” በማለት በቊጣ ገሠጽኳቸው። ለችግሩም መፍትሔ ለማግኘት ሕዝቡን በአንድነት ሰብስቤ “ለአሕዛብ ሕዝቦች የተሸጡ አይሁድ ወገኖቻችንን ራሳችን ልንቤዣቸው በማሰብ የሚቻለንን ሁሉ አደረግን፤ እናንተ ደግሞ እነሆ፥ የገዛ ወንድሞቻችሁ የሆኑት አይሁድን ወገኖቻቸው ለሆናችሁት ለእናንተ ባርያዎች አድርገው ራሳቸውን እንዲሸጡላችሁ በማድረግ ላይ ትገኛላችሁ!” ብዬ ገሠጽኳቸው፤ መሪዎቹም የሚመልሱት ቃል አጥተው ዝም አሉ።
ነህምያ 5:6-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እኔም ጩኸታቸውንና እነዚህን ቃላት በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቆጣሁ። በልቤም አሰብሁና መኳንንቶቹንና ሹማምቱን ተከራከርኋቸው፥ እንዲህም አልኋቸው፦ “እያንዳንዳችሁ ለወንድማችሁ በአራጣ ታበድራላችሁ”፤ ትልቅ ጉባኤም ሰበሰብሁባቸው። እኔም እንዲህ አልኳቸው፦ “ለአሕዛብ የተሸጡትን አይሁድ ወንድሞቻችንን በተቻለን መጠን ተቤዠን፥ እናንተ ደግሞ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁ? እነርሱስ ለእኛ ይሸጣሉን? እነርሱም ዝም አሉ፥ የሚመልሱትንም ቃል አጡ።