ሉቃስ 6:43-46
ሉቃስ 6:43-46 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ክፉ ፍሬን የሚያፈራ መልካም ዛፍ የለም፤ መልካም ፍሬ የሚያፈራ ክፉ ዛፍም የለም። ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾህ በለስን አይለቅሙም፤ ከደንደርም ወይንን አይለቅሙም። መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካምን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከልቡ ክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል፤ ከልብ የተረፈውን አፍ ይናገራልና። “ለምን አቤቱ፥ አቤቱ፥ ትሉኛላችሁ? የምላችሁንም አታደርጉም።
ሉቃስ 6:43-46 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“መልካም ዛፍ ሆኖ ሳለ መጥፎ ፍሬ የሚያፈራ የለም፤ እንዲሁም መጥፎ ዛፍ ሆኖ መልካም ፍሬ የሚያፈራ የለም። ዛፍ ሁሉ በፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾኽ የበለስ ፍሬ አይለቀምም፤ ከቀጋ ቍጥቋጦ የወይን ፍሬ አይቈረጥም። መልካም ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ካከማቸው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና። “እኔ የምለውን አታደርጉም፤ ታዲያ ለምን፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ’ ትሉኛላችሁ?
ሉቃስ 6:43-46 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ክፉ ፍሬ የሚያደርግ መልካም ዛፍ የለምና፥ እንዲሁም መልካም ፍሬ የሚያደርግ ክፉ ዛፍ የለም። ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፥ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን አይቈርጡም። በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል። ስለ ምን፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ትሉኛላችሁ፥ የምለውንም አታደርጉም?
ሉቃስ 6:43-46 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“መልካም ዛፍ መጥፎ ፍሬ አያፈራም፤ እንዲሁም መጥፎ ዛፍ መልካም ፍሬ አያፈራም። ዛፍ ሁሉ በፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾኽ የበለስ ፍሬ አይለቀምም፤ እንዲሁም ከእሾኻማ ቊጥቋጦ የወይን ፍሬ አይለቀምም። ስለዚህ ደግ ሰው ከመልካም ልቡ መልካምን ነገር ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከመጥፎ ልቡ ክፉውን ነገር ያወጣል። ሰው በአፉ የሚናገረው ከልቡ ሞልቶ የተረፈውን ነው። “እኔ የምነግራችሁን አትፈጽሙም፤ ታዲያ፥ ስለምን ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! እያላችሁ ትጠሩኛላችሁ?
ሉቃስ 6:43-46 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
መልካም ዛፍ የተበላሸ ፍሬ አያፈራምና፤ እንዲሁም የተበላሸ ዛፍ መልካም ፍሬ አያፈራም። ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፤ ከአጣጥ ቁጥቋጦም ወይን አይቈርጡም። መልካም ሰው በልቡ ከሚገኘው መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሚገኘው ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል፤ በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና። ስለምን “ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ትሉኛላችሁ? የምለውን ግን አታደርጉም?