ሐዋርያት ሥራ 13:1-12
ሐዋርያት ሥራ 13:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በአንጾኪያ በነበረችው ቤተ ክርስቲያንም ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉቅዮስ፥ ከአራተኛው ክፍል ገዢ ከሄሮድስ ጋር ያደገው ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ፥ ሲጾሙም መንፈስ ቅዱስ፥ “በርናባስንና ሳውልን እኔ ለፈለግኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አላቸው። ያንጊዜም ከጾሙና ከጸለዩ፥ እጃቸውንም በራሳቸው ላይ ከጫኑባቸው በኋላ ላኩአቸው። ከመንፈስ ቅዱስም ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። ወደ ሰልሚና ሀገርም ገብተው በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስም እየአገለገላቸው ከእነርሱ ጋር ነበር። በደሴቲቱም ሁሉ ሲዘዋወሩ ጳፉ ወደምትባል ሀገር ደረሱ፤ በዚያም አንድ አይሁዳዊ የሆነ ሐሰተኛ ነቢይና አስማተኛ ሰው አገኙ፤ ስሙም በርያሱስ ይባላል። እርሱም ብልህ ሰው በሆነ ሰርግዮስ ጳውሎስ በሚባል አገረ ገዢ ዘንድ ይኖር ነበረ። የእግዚአብሔርንም ቃል ሊሰማ ወድዶ በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠራቸው። አስማተኛው ኤልማስም የስሙ ትርጓሜ እንዲህ ነበረና፥ ገዥውን ከማመን ሊከለክለው ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ በተባለው በሳውል ላይም ቅዱስ መንፈስ ሞላበት፤ አተኵሮም ተመለከተው። እንዲህም አለው፥ “ሽንገላንና ክፋትን ሁሉ የተመላህ፥ የሰይጣን ልጅ፥ የጽድቅ ሁሉ ጠላት ሆይ፥ የቀናውን የእግዚአብሔርን መንገድ ማጣመምህን ትተው ዘንድ እንቢ አልህን? እነሆ፥ አሁን የእግዚአብሔር እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤” ወዲያውኑም ታወረ፤ ጨለማም ዋጠው፤ የሚመራውም ፈለገ። አገረ ገዢውም የሆነውን በአየ ጊዜ ተገረመ፤ በጌታችን ትምህርትም አመነ።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፣ ኔጌር የተባለው ስምዖን፣ የቀሬናው ሉክዮስ፣ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስ ዐብሮ አደግ የነበረው ምናሔ እና ሳውል ነበሩ። እነዚህም ጌታን እያመለኩና እየጾሙ ሳሉ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ “በርናባስንና ሳውልን እኔ ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አለ። እነርሱም ከጾሙና ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጭነው አሰናበቷቸው። በርናባስና ሳውልም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። ስልማና በደረሱም ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ ዮሐንስም እንደ አገልጋያቸው ዐብሯቸው ነበር። የቆጵሮስን ደሴት ከዳር እስከ ዳር አቋርጠው ጳፉ በደረሱ ጊዜ፣ በርያሱስ የተባለ አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ አገኙ፤ እርሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አስተዋይ አገረ ገዥ ጋራ ነበረ። ይህ አገረ ገዥ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን አስጠራቸው። ጠንቋዩ ኤልማስ ግን፣ የስሙ ትርጕም እንዲህ ነበርና፣ አገረ ገዥው እንዳያምን ለማደናቀፍ ስለ ፈለገ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለውም ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ፣ ትኵር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፤ “አንተ የጽድቅ ሁሉ ጠላት፣ ተንኰልንና ክፋትን ሁሉ የተሞላህ የዲያብሎስ ልጅ፣ የጌታን ቀና መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም የጌታ እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውር ትሆናለህ፤ ከእንግዲህ የፀሓይን ብርሃን ለአንድ አፍታ እንኳ አታይም።” ወዲያውም ጭጋግና ጨለማ በላዩ ወረደ፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ለመፈለግ ወዲያ ወዲህ ይል ጀመር። አገረ ገዥውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ በጌታ ትምህርት በመደነቅ አመነ።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርሲቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ “በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው። ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ ሲመለከተው፦ “አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም” አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያት ተብለው የሚጠሩ ሰባኪዎችና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፥ ጥቊር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉክዮስ፥ የአራተኛው ክፍል ገዢ የሄሮድስ አብሮ ዐደግ የነበረው ምናሔና ሳውል ነበሩ። እነርሱ ጌታን ሲያገለግሉና ሲጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ “እኔ ለመረጥኳቸው ሥራ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ!” አለ። እነርሱም ጾመውና ጸልየው እጆቻቸውን ከጫኑባቸው በኋላ ላኳቸው። በርናባስና ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ሄዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ተጓዙ። ወደ ሰላሚስ ከተማ በደረሱ ጊዜ በአይሁድ ምኲራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስ ማርቆስም ከእነርሱ ጋር ሆኖ ይረዳቸው ነበር። የቆጵሮስን ደሴት አቋርጠው ወደ ጳፉ በደረሱ ጊዜ ባርየሱስ የሚባለውን አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይ አገኙ፤ እርሱ ሐሰተኛ ነቢይ ነበር። የሚኖረውም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አስተዋይ አገረ ገዢ ጋር ነበረ፤ ይህ አገረ ገዢ በርናባስንና ሳውልን አስጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈለገ። ነገር ግን በግሪክ ቋንቋ “ኤሊማስ” ተብሎ የሚጠራው ጠንቋይ ባርየሱስ አገረ ገዢው እንዳያምን ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፦ “አንተ የዲያብሎስ ልጅ! የእውነት ሁሉ ጠላት! ማታለልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፥ ቀጥተኛውን የጌታን መንገድ ማጣመም አትተውምን! አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ ይመታሃል፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ ለጥቂት ጊዜም የፀሐይን ብርሃን አታይም።” ወዲያውኑ ዐይኖቹን ጭጋግና ጨለማ ሸፈናቸው፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ። አገረ ገዢውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ አመነ፤ ስለ ጌታ በሰማውም ትምህርት ተደነቀ።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርሲቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ “በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ፤” አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው። ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኩር ብሎ ሲመለከተው “አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፤ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤” አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፤ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዢው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ።