ትንቢተ ሕዝቅኤል 14:1-9

ትንቢተ ሕዝቅኤል 14:1-9 አማ54

ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል። የበደላቸውንም መቅሠፍት በፊታቸው አቁመዋል፥ እኔስ ከእነርሱ ልጠየቅን? ስለዚህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁሉም በጣዖቶቻቸው ከእኔ ተለይተዋልና የእስራኤልን ቤት በልባቸው እይዝ ዘንድ ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ ብለህ ንገራቸው። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ንስሐ ግቡ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ፊታችሁንም ከርኵሰታችሁ ሁሉ መልሱ። ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ፥ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ፥ ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ ከሕዝቤም መካከል አጠፋዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። ነቢዩም ቢታለል ቃልንም ቢናገር፥ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እጄንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ ከሕዝቤም ከእስራኤል መካከል አጠፋዋለሁ።