አማትዋም ኑኃሚን አለቻት፦ ልጄ ሆይ፥ መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈልግልሽምን? አሁንም ከገረዶቹ ጋር የነበርሽበት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል። እንግዲህ ታጠቢ፥ ተቀቢ፥ ልብስሽን ተላበሺ፥ ወደ አውድማውም ውረጂ፣ ነገር ግን መብሉንና መጠጡን እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታዪው። በተኛም ጊዜ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም እግሩን ግለጪ፥ ተጋደሚም፣ የምታደርጊውንም እርሱ ይነግርሻል። ሩትም፦ የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለቻት። ወደ አውድማውም ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች። ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፣ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች። መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፣ እነሆም፥ አንዲት ሴት በእግርጌው ተኝታ ነበረች። እርሱም፦ ማን ነሽ? አለ። እርስዋም፦ እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፣ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ አለችው። ቦዔዝም አላት፦ ልጄ ሆይ፥ በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፣ ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት አድርገሻል። አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ አትፍሪ፣ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ።
መጽሐፈ ሩት 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሩት 3:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች