የዮሐንስ ራእይ 21:15-27
የዮሐንስ ራእይ 21:15-27 መቅካእኤ
የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው። ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፤ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት፤ ሁለት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ሜትር ሆነች፤ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው። ቅጥርዋንም ለካ፤ በመልአኩ በሚለካበት በሰው መለኪያ መቶ አርባ አራት ክንድ ነበር፤ ቅጥርዋም ከኢያሰጲድ የተሠራ ነበረ፤ ከተማይቱም የጠራ ብርጭቆ የሚመስል ንጹሕ ወርቅ ነበረች። የከተማይቱም ቅጥር መሠረቶች በከበረ ድንጋይ ሁሉ ያጌጦ ነበር፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ፥ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥ አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፥ ዐሥረኛው ክርስጵራስስ፥ ዐሥራ አንደኛው ያክንት፥ ዐሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ። ዐሥራ ሁለቱም ደጆች ዐሥራ ሁለት ዕንቁዎች ነበሩ፤ እያንዳንዱም ደጅ ከአንድ ዕንቁ የተሠራ ነበረ። የከተማይቱም መንገድ እንደ መስታወት ብርሃን ከሚያስተላልፍ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበረ። ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ስለ ሆኑ በእርሷ ዘንድ መቅደስ አላየሁም። ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት፥ መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር። አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፤ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርሷ ያመጣሉ፤ በዚያም ሌሊት ስለ ሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፤ የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርሷ ያመጣሉ። ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኩሰትና ውሸትም የሚያደርግ ሁሉ ወደ እርሷ ከቶ አይገባም።

