የሉቃስ ወንጌል 1:1-7

የሉቃስ ወንጌል 1:1-7 መቅካእኤ

እጅግ የተከበርክ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ብዙዎች በእኛ መካከል ስለ ተፈጸሙት ክስተቶች በጽሑፍ ለማዘጋጀት እንደሞከሩት ሁሉ፥ ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት ለእኛ ባስተላለፉልን መሠረት፥ ከመጀመሪያው አንሥቶ ስለሆኑት ነገሮች ሁሉ በጥንቃቄ በመመርመር፥ ለአንተ ቅደም ተከተሉን የጠበቀ ታሪክ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ። በዚህም ስለ ተማርካቸው ነገሮች እርግጠኛነት በደንብ እንድታውቅ ብዬ ነው። በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱም ከአሮን ሴት ልጆች ወገን ነበረች፤ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ በጌታ ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ ይመላለሱ ነበር። ኤልሳቤጥም መካን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜያቸው አርጅተው ነበር።