ትንቢተ ኢሳይያስ 65:17-23
ትንቢተ ኢሳይያስ 65:17-23 መቅካእኤ
እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁ፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ትውስታቸውም አይኖርም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘለዓለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም። ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጎልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ የመቶ ዓመት ሳይሆነው የሚሞት እንደተረገመ ኃጢአተኛ ይታያል። ቤትም ይሠራሉ ይኖሩበታል፤ ወይንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፥ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል። እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።

