የማቴዎስ ወንጌል 5:21-30

የማቴዎስ ወንጌል 5:21-30 አማ05

“በቀድሞ ጊዜ ለነበሩ ሰዎች የተባለውን ሰምታችኋል፤ ይኸውም ‘አትግደል፤ ሰውን የገደለ ይፈረድበታል’ የሚል ነው። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ የሚቈጣ ሁሉ ይፈረድበታል፤ ደግሞም ወንድሙን፥ ‘አንተ የማትረባ!’ ብሎ የሚሳደብ በሸንጎ ይፈረድበታል፤ ‘ደደብ!’ ብሎ የሚሳደብ ሁሉ በገሃነመ እሳት ይፈረድበታል። ስለዚህ አንተ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ፥ ያዘነብህ ወንድም መኖሩን ብታስታውስ፥ መባህን በመሠዊያው ፊት አስቀምጥና፥ ሄደህ በመጀመሪያ ከዚያ ከወንድም ጋር ታረቅ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰህ መባህን አቅርብ። ባላጋራህ ከሶህ ከእርሱ ጋር ወደ ፍርድ ቤት ስትሄድ በመንገድ ላይ ሳለህ ቶሎ ብለህ ከባላጋራህ ጋር ተስማማ። አለበለዚያ ባላጋራህ ለዳኛ፥ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ ይሰጥህና ወደ ወህኒ ቤት ትገባለህ። በእውነት እልሃለሁ፥ የተፈረደብህን የመጨረሻዋን ሳንቲም ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘አታመንዝር!’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ‘ሴትን ተመልክቶ የተመኛት ሁሉ፥ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመነዘረ’ እላችኋለሁ። የቀኝ ዐይንህ ለኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ አውጥተህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ ቈርጠህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች