የሐዋርያት ሥራ 25:13-27

የሐዋርያት ሥራ 25:13-27 አማ05

ከጥቂት ቀን በኋላ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ፊስጦስን “እንኳን ደኅና መጣህ” ለማለት ወደ ቂሳርያ መጡ። እዚያም ብዙ ቀን በመቀመጣቸው ፊስጦስ የጳውሎስን ጉዳይ እንዲህ ሲል ለንጉሥ አግሪጳ ገለጠ፤ “ፊልክስ አስሮ የተወው እዚህ አንድ ሰው አለ፤ እኔ በኢየሩሳሌም በነበርኩበት ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች የዚህን ሰው ጉዳይ ካመለከቱኝ በኋላ እንድፈርድበት ጠየቁኝ። እኔ ግን ‘ተከሳሽ ከከሳሾች ፊት ቆሞ ለተከሰሰበት ነገር የመከላከያ መልስ ሳይሰጥ ተከሳሹን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም’ ብዬ መለስኩላቸው። ስለዚህ ከሳሾቹ ተሰብስበው ወደዚህ በመጡ ጊዜ ሳልዘገይ በማግስቱ በፍርድ ወንበር ተቀመጥሁና ጳውሎስን በፊቴ እንዲያቀርቡት አዘዝኩ፤ ከሳሾቹም ለመናገር አጠገቡ በቆሙ ጊዜ እኔ ክፉ ነገር ሠርቶአል ብዬ የገመትኩትን ያኽል ለክስ የሚያበቃ ምንም ነገር አላቀረቡበትም። ነገር ግን ከእርሱ ጋር ይከራከሩበት የነበረው ስለ ሃይማኖታቸውና ሞቶ ስለ ነበረው ጳውሎስ ግን ‘ሕያው ነው’ ስለሚለው ኢየሱስ ነው። እኔም እንዲህ ዐይነቱን ነገር መመርመር ስለ ቸገረኝ ጳውሎስን ‘ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ እዚያ በዚህ ነገር ልትፋረድ ትወዳለህን?’ አልኩት። እርሱ ግን ጉዳዩ በሮም ንጉሠ ነገሥት እንዲታይለት ፈልጎ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ይግባኝ በማለቱ ወደ እዚያ እስክልከው ድረስ በእስር ቤት እንዲቈይ አዘዝኩ።” አግሪጳም ፊስጦስን “እኔም ይህ ሰው ሲናገር መስማት እፈልጋለሁ” አለው። ፊስጦስም “ነገ ትሰማዋለህ” አለው። ስለዚህ በማግስቱ አግሪጳና በርኒቄ ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰውና በታላቅ ግርማ ሆነው በጦር አለቆችና በከተማው ታላላቅ ሰዎችም ታጅበው መጡና ወደ ፍርድ አዳራሽ ገቡ፤ ከዚያም በኋላ ፊስጦስ ጳውሎስን አስጠራ። እንዲህም አለ፤ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ሰዎች ሁሉ! አይሁድ ‘ይህ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት መኖር አይገባውም’ በማለት እየጮኹ በኢየሩሳሌምም፥ በዚህም እንዲፈረድበት የጠየቁኝ ይህ የምታዩት ሰው ነው። እኔ ግን በሞት የሚያስቀጣው ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ እርሱ ወደ ሮም ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ በማለቱ ወደዚያ ልልከው ወሰንኩ። ይሁን እንጂ ስለ እርሱ ለጌታዬ የምጽፈው የተረጋገጠ ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈው ነገር እንዳገኝ ብዬ በፊታችሁ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! በፊትህ አቅርቤዋለሁ። እስረኛ ወደ በላይ ሲላክ፥ የተከሰሰበትን ምክንያት አለመግለጥ ሞኝነት መስሎ ታይቶኛል።”