ሉቃስ 23:27-38

ሉቃስ 23:27-38 NASV

ብዙ ሕዝብና ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶችም ከኋላው ይከተሉት ነበር። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፤ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔ አታልቅሱ፤ እነሆ፤ ‘መካኖችና ያልወለዱ ማሕፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው’ የምትሉበት ጊዜ ይመጣልና። በዚያ ጊዜ፣ “ ‘ተራሮችን፣ “ውደቁብን!” ኰረብቶችንም፣ “ሸፍኑን!” ’ ይላሉ። እንግዲህ በርጥብ ዕንጨት እንዲህ ካደረጉ፣ በደረቁ ምን ያደርጉ ይሆን?” ከርሱ ጋራ እንዲገደሉ ሌሎች ሁለት ወንጀለኞችን ወሰዷቸው። ቀራንዮ የተባለ ቦታ በደረሱ ጊዜ ሰቀሉት፤ ወንጀለኞቹንም አንዱን በቀኙ፣ ሌላውን በግራው ሰቀሏቸው። ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። ገዦችም፣ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስኪ ራሱን ያድን” እያሉ አፌዙበት። ወታደሮችም ቀርበው ያፌዙበት ነበር፤ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ እየሰጡትም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህ፣ ራስህን አድን” ይሉት ነበር። ከራሱም በላይ፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍ ነበር።