ሕዝቅኤል 19
19
ስለ እስራኤል መሳፍንት የወጣ ሙሾ
1“ስለ እስራኤል መሳፍንት ሙሾ አውጣ፤ 2እንዲህም በል፤
“ ‘እናትህ በአንበሶች መካከል እንዴት
ያለች አንበሳ ነበረች!
በደቦል አንበሶች መካከል ተጋደመች፤
ግልገሎቿንም በዚያ አሳደገች።
3ከግልገሎቿ መካከል አንዱን አሳደገችው፤
እርሱም ብርቱ አንበሳ ሆነ።
ግዳይ መንጠቅን ተማረ፤
ሰዎችንም በላ።
4አሕዛብም ስለ እርሱ ሰሙ፤
በጕድጓዳቸውም ገብቶ ተያዘ፤
እነርሱም በስናግ ጐትተው፣
ወደ ግብጽ ምድር ወሰዱት።
5“ ‘ተስፋዋ መጨናገፉን፣
የጠበቀችውም አለመሳካቱን ባየች ጊዜ፣
ከግልገሎቿ ሌላውን ወስዳ፣
ብርቱ አንበሳ አድርጋ አሳደገችው።
6እርሱም በአንበሶች መካከል ተጐማለለ፤
እየበረታም ሄደ፤
ግዳይ መንጠቅን ተማረ፤
ሰዎችንም በላ።
7ምሽጎቻቸውን አወደመ፤#19፥7 ከታርጕም (ሰብዓ ሊቃናት ይመ) ጋራ ተመሳሳይ ሲሆን፣ ዕብራይስጡ ግን ምሽጎቻቸውን ያውቃል ይላል።
ከተሞቻቸውንም ባድማ አደረገ፤
ምድሪቷና በውስጧ ያሉት ሁሉ፣
ከግሣቱ የተነሣ ተንቀጠቀጡ።
8በዙሪያው ያሉ አሕዛብ ተነሡበት፤
ከየአገሩም ሁሉ ተሰበሰቡበት፤
መረባቸውን ዘረጉበት፤
በጕድጓዳቸውም ገብቶ ተያዘ።
9በስናግም በመጐተት ቀፎ ውስጥ ከትተው፣
ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጡት፤
ድምፁ በእስራኤል ተራሮች ላይ፣
ዳግመኛ እንዳይሰማ፣
በእስር ቤት አኖሩት።
10“ ‘እናትህ በውሃ አጠገብ የተተከለ፣
በዕርሻ ውስጥ ያለ፣#19፥10 ከሁለት የጥንት የዕብራይስጥ ቅጆች ጋራ ተመሳሳይ ሲሆን አብዛኛዎቹ የጥንት ቅጆች ግን ያንተ ደም ይላሉ።
ከውሃም ብዛት የተነሣ፣
ያፈራና የተንሰራፋ የወይን ተክል
መሰለች።
11ቅርንጫፎቿ ለበትረ መንግሥት
የሚሆኑ፣ ጠንካሮች ነበሩ፤
ጥቅጥቅ ባሉ ቅጠሎች መካከል፣
በቁመቷና በብዙ ቅርንጫፎቿ፣
ዘለግ ብላ፣ ጐልታ ትታይ ነበር።
12ነገር ግን በቍጣ ተነቀለች፤
ወደ ምድርም ተጣለች።
የምሥራቅ ነፋስ አደረቃት፤
ፍሬዎቿንም አረገፈባት።
ብርቱዎቹ ቅርንጫፎቿ ክው አሉ፤
እሳትም በላቸው።
13አሁን ውሃ በተጠማ ደረቅ ምድር፣
በበረሓ ውስጥ ተተከለች።
14ከዋና ቅርንጫፎቿ#19፥14 ወይም ከዋና ቅርንጫፎቿ ሥር ከአንዱ እሳት ወጣ፤
ፍሬዋንም በላ።
በትረ መንግሥት የሚሆን፣
አንድም ጠንካራ ቅርንጫፍ አልተረፈም።’
ይህ ሙሾ ነው፤ ለሐዘን እንጕርጕሮም ይሆናል።”
Currently Selected:
ሕዝቅኤል 19: NASV
ማድመቅ
ኮፒ
አወዳድር
ያጋሩ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.